ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ አልሸባብን የመዋጋት ዘመቻን ለማጠናከር በተካሄደው ቀጣናዊ መድረክ ላይ ተሳተፉ

ጥር 24/2015 (ዋልታ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በምስራቅ አፍሪካ አልሸባብን የመዋጋት ዘመቻን ለማጠናከር በተካሄደው ቀጣናዊ መድረክ ላይ ተሳትፈዋል፡፡

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በተጨማሪ የሶማሊያ፣ ኬንያ እና ጅቡቲ መሪዎች የተሳፈፉ ሲሆን መሪዎቹ በውይይታቸው ለቀጣናዊ ችግሮች ቀጣናዊ መፍትሄ መስጠትን ያለመ ምክክር ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም የአሸባሪውን አልሸባብ እንቅስቃሴ ለመግታት የቀጣናውን ሀገራት ትብብር ማጠናከር እንደሚገባ መጠቆሙን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሶማሊያ የሚገኘው የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ተልዕኮ አካል በመሆን አልሸባብን እየተዋጉ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ወታደሮች ጋርም መወያየታቸው ተጠቁሟል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምስራቅ አፍሪካ አልሸባብን የመዋጋት ዘመቻን ለማጠናከር በሶማሊያ በተካሄደው ቀጣናዊ መድረክ ለመሳተፍ በዛሬው ዕለት ሞቃዲሾ መግባታቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡