ጠ/ሚ ዐቢይ ከተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ ጋር ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን ድጋፍ ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተወያዩ

የካቲት 11/2015 (ዋልታ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ጎን ለጎን  ከተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ጋር ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን ድጋፍ ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተወያዩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው “የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ወደ ኢትዮጵያ እንኳን ደኅና መጡ” ብለዋል፡፡

በዚህም ከአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ጎን ለጎን ባደረጉት የሁለትዮሽ ውይይት በሰላም ስምምነቱ አተገባበር እንዲሁም የመንግሥታቱ ድርጅት ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን ድጋፍ የበለጠ ማሳደግ በሚቻልበት ዙሪያ መወያየታቸውን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት አኪንዉሚ አድሲና (ዶ/ር) ጋር መገናኘታቸውን አስታውቀዋል።

የልማት ባንኩ ለግብርና ክፍለ ኢኮኖሚያችን በተለይ ለስንዴ ምርታማነት ጥረታችን እና ለሌሎች ቁልፍ ምርቶቻችን የሚያደርገው ያልተቋረጠ ድጋፍ ወሳኝ ነው ሲሉም በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው ላይ አስፍረዋል።