አፍሪካ ባለፉት 3 ዓመታት አስቸጋሪ የኢኮኖሚ ሂደቶች ማሳለፏ ተገለጸ

የካቲት 11/2015 (ዋልታ) አፍሪካ ባለፉት 3 ዓመታት አስቸጋሪ የኢኮኖሚ ሂደቶች ማሳለፏ እና የዋጋ ግሽበት ትልቁ ተግዳሮት እንደሆነባት ተገለጸ፡፡

36ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ “የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ትግበራን ማፋጠን” በሚል እና በሌሎች አህጉራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መሪዎቹ ወይይት አድርገዋል፡፡

በውይይቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ በሚል በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሓት መካከል በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት የተፈረመው የሰላም ስምምነት የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል::

አፍሪካ ባለፉት 3 ዓመታት አስቸጋሪ የኢኮኖሚ ሂደቶችን ማሳለፏን እና የዋጋ ግሽበት ትልቁ ተግዳሮት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል በ2023 በአፍሪካ በዋናነት በአህጉሪቱ የተረጋጋ ኢኮኖሚ ለመፍጠር ትላልቅ መሰረተ ልማቶች እና የፋይናንስ ተቋማት መገንባታቸውን ጠቁመው በ2023 ተኩስ የማይሰማባት አፍሪካን ለመፍጠር ፍኖተ ካርታ በህብረቱ ተዘጋጅቶ እየተሰራበት እንዳለ ተናግረዋል፡፡

በጉባኤው ላይ ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ጦርነት ውስጥ እንደነበረች ገልጸው ግጭቱ አፍሪካዊ መፍትሄ እንዲያገኘ በአፍሪካ ህብረት አሸማጋይነት ከህወሓት ጋር ስምምነት መፈረሙን ጠቅሰዋል:: ይህም ኢትዮጵያ ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ የሚለውን እሳቤ በተግባር ያሳየችበት ነው ብለዋል::

በተጨማሪም ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያ እንዲሁም በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ያሉ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ እንዲያገኙ ስትሰራ መቆየቷን እና ወደፊትም እንደምትሰራ ገልጸዋል።

ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን ለማሳደግ የግብርና ስራ ላይ ትኩረት በማደረግ ስትሰራ በመቆየት በስንዴ ምርት ከፍተኛ ውጤት ማግኘቷን አመላክተው ከሀገር ውስጥ ሽፋን ባለፈ ወደ ወጪ ለመላክ ዝግጆቿን ማጠናቀቋን እና ወደ ስራ መገባቱን ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ አፍሪካን ለመመገብ የሚያስችላትን ስራ በግብርናው ዘርፍ አጠናክራ እየሰራች እንደምትገኝ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከዚህ ባለፈ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ከ25 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ችግሩን ለመቋቋም በሚገባ መስራቷን አብራርተዋል።

በተጨማሪም የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ምስረታ ትግበራ ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረው አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ሊኖራት ይገባል ሲሉም በአጽንኦት አንስተዋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በበኩላቸው ነፃ የንግድ ቀጣና ምስረታ ላይ በአፍሪካ እየተሰራ ያለው ስራ አስደሳች መሆኑን ጠቅሰው የተባበሩት መንግስታት በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ምስረታ ላይ ከአፍሪካ ኅብረት ጋር በጋራ በመስራቱ ደስተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የአፍሪካ አህጉርን ኢኮኖሚ ለመቀየር እና ለማሳደግ የሚያስችል እምቅ የተፈጥሮ ሀብት እንዳለም ጠቁመዋል::

በዓለም ላይ ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል በደቡብ አፍሪካ፣ ኮንጎ እና ኢትዮጵያ እንዲሁም በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የተሰራው ስራ አስደሳች እንደሆነም አመላክቷል፡፡

በሜሮን መስፍን