ጣናነሽ ፪ ወደ ሀገር ቤት እያቀናች ነው

ጣናነሽ ፪

የካቲት 29/2016 (አዲስ ዋልታ) በኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ለ‘ኢትዮ ፌሪስ ጣና’ የሀገር ውስጥ የውሃ ትራንስፖርት እንዲያገለግሉ የተገዙት ሁለት ዘመናዊ ጀልባዎች ወደ ሀገር ቤት እያቀኑ ነው።

ጣናነሽ ፪ የተሰኘችውን ዘመናዊ የህዝብ ትራንስፖርት ጀልባና ሌላኛዋን መለስተኛ ፈጣን ቃኚ ጀልባ በአሶሳ መርከብ ላይ የመጫኑ ስራ የተጠናቀቀ ሲሆን ከቀናት ጉዞ በኋላ መጋቢት 24 ጅቡቲ ወደብ እንደሚደርሱ ይጠበቃል።

ጣናነሽ ፪ ዘመናዊ የሰው ማጓጓዣ እና የመዝናኛ መርከብ ስትሆን 38 ሜትር ርዝመት እንዳላትም ተገልጿል።

በአንድ ጊዜ 188 ሰዎችን የመጫን አቅም ያላት ጣናነሽ ለጣና የውሃ ላይ ትራንስፖርት ተጠቃሚዎች ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት የምትሰጥ መሆኑን የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ መረጃ አመላክቷል።

በ1942 ዓ.ም ጣሊያናዊያንና ኢትዮጵያዊያን ግለሰቦች ተሰባስበው የባህር ትራንስፖርት ድርጅት ሲያቋቁሙ ‘ናቪጋ ጣና’ የሚል ስያሜ የነበረው ድርጅት በኋላ መንግሥት ተረክቦት የጣና ሐይቅ ትራንስፖርት ድርጅት በሚል ስራውን ሲያከናውን ቆይቷል።

አሁን ከኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ጋር ተዋህዶ ‘ኢትዮ ፌሪስ ጣና’ በሚል ስያሜ ብቅ ላለው ድርጅት እርሾው ‘ናቪጋ ጣና’ ነበር።