የሴቶች ቀን ለምን ይከበራል?

የዓለም የሴቶች ቀን

የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) መረጃ እንደሚያመላክተው በ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ አካባቢ በሰሜን አሜሪካ እና በአውሮፓ የተከሰተውን የሴት ሰራተኞች እንቅስቃሴ ተከትሎ የዓለም የሴቶች ቀን ጽንሰ ሀሳብ ብቅ ብሏል።

እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1908 በኒውዮርክ ከተማ ሴት የጋርመንት ሰራተኞች በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ከባድ የስራ ጫና ተከትሎ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል። በወቅቱ የሥራ ሰዓት መሻሻልን፣ የተሻለ ክፍያንና ሴቶች በምርጫ መሳተፍ አለባቸው የሚሉትና መሰል ሀሳቦችን በማንገብ ነበር የተቃውሞ ሰልፍ ያከሄዱት።

ይህንንም ተከትሎ ከአንድ ዓመት በኋላ እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር በየካቲት 28/1909 ብሔራዊ የሴቶች ቀን እንዲኖር ተወስኗል።

ጀርመናዊት የሴቶች መብት ተሟጋቿ “ክላራ ዜትኪን” ቀኑ ዓለም አቀፋዊ እንዲሆን ሀሳብ ያመነጨችው በዴንማርኳ ኮፐንሃገን በአውሮፓውያኑ 1910 የሴት ሠራተኞች ዓለም አቀፍ ጉባኤ በተካሄደበት ዕለት ነበር።

እ.ኤ.አ. በ1945 በተባበሩት መንግስታት ቻርተር በወንዶች እና በሴቶች መካከል የእኩልነት መርህን ለማረጋገጥ የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ ስምምነት ተደረገ። በፈረንጆቹ መጋቢት 8/1975 የሴቶች ቀን በተባበሩት መንግስታት በይፋ ተከበረ።

ከሁለት ዓመታት በኋላ የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ተወያይቶ ካሳለፈው ውሳኔ በኋላ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ዓለም አቀፍ በዓል ሆኖ በአባል ሀገራቱ በየዓመቱ መጋቢት 8 እንዲከበር ተደርጓል። ከዚያ እለት ጀምሮም በየዓመቱ እየተከበረ ይገኛል።

ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን የስርዓተ ጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥ የሚረዱ መልዕክቶችን ለማስተላለፍ፣ ግንዛቤ ለማስጨበጥ እና ከስርዓተ-ፆታ አድልዎ የፀዳ የተሻለ ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚሉ ሀሳቦችን በማራመድ ይከበራል፡፡

በተጨማሪም ሴቶችን ለማክበር፣ የሴቶች እኩል መብትን ለማረጋገጥ፣ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል ያለሙ መልዕክቶች ለማስተላለፍ የበዓሉ መከበር አስፈላጊ መሆኑም ይጠቀሳል።

ዓለም አቀፍ ሴቶች ቀን በተለያዩ ሀገራት የተለያዩ ስጦታዎችን በመሰጣጠትና የተለያዩ ሥርዓቶችን በማካሄድ ይከበራል፡፡ በሴት ደራሲያን የተፃፉ መጻሕፍትን ስጦታ በማበርከት፣ ስለ ሴቶች መብት እና የፆታ እኩልነት በማስተማር፣ የሚወዷቸውን በሴቶች የተደረሱ ፊልሞችን በመመልከት እና በሌሎችም ሴቶችን የሚያበረታቱ ተግባራት በመከወን ያከብራሉ።

በቻይና በዕለቱ ሴት ሰራተኞች ግማሽ ቀን ብቻ እንዲሰሩ ይፈቀዳል፡፡ በጣልያን “ላ ፌስታ ዴላ ዶና” ተብሎ የሚጠራው ይህ ዕለት “ሚሞሳ” ተብላ የምትጠራውን አበባ ስጦታ በመለዋወጥ ያከብሩታል፡፡ በአሜሪካ ሙሉ የማርች ወር የሴቶች ታሪክ ወር የሚል ዕውቅና ይሰጣል። በአገሪቱ መሪዎች ዘንድም ዕውቅና በተሰጠው በዚህ ወር የአሜሪካ ሴቶች አስተዋፅኦ ይዘከራል።

የዘንድሮ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን “ሴቶችን እናብቃ፤ ልማትና ሰላምን እናረጋግጥ” በሚል መሪ ቃል በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ113ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ43ኛ ጊዜ ይከበራል።

የሴቶች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ በፈረንጆቹ መጋቢት 8 ተከብሮ ይውላል። በዚህም በየዓመቱ መጋቢት 8 በብዙ አገራት ብሔራዊ በዓል ወደመሆንም ደርሷል።

በአዲስዓለም ግደይ