ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በኬኒያ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ህልፈት የተሰማቸውን ሃዘን ገለጹ

ጀኔራል ፍራንሲስ ኦሞንዲ ኦጎላን

ሚያዝያ 11/2016 (አዲስ ዋልታ) የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የኬኒያ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጀኔራል ፍራንሲስ ኦሞንዲ ኦጎላን ህልፈተ-ሕይወት የተሰማቸውን ሃዘን ገለጹ።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ባስተላለፉት የሃዘን መግለጫ ጀኔራል ፍራንሲስ ኦሞንዲ ኦጎላ ለሀገራቸውና ለቀጣናው ሠላምና ደህንነት መረጋገጥ የነበራቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደነበር አስታውቀዋል።

እሳቸውና ሌሎች ከፍተኛ መኮንኖችን ባጋጠመቸው የሄሊኮፕተር መከስከስ አደጋ ህይወታቸው በማለፉ በራሳቸውና በኢ.ፌ.ዲ.ሪ መከላከያ ሠራዊት ስም የተሰማቸውን ሃዘን መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ጀኔራል ፍራነኪስ ኦሞንዲ ኦጎላ ለኬኒያና ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ላበረከቱት አስተዋጽኦና በጎ ሥራ ሁልጊዜ ሲታወሱ ይኖራሉ ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከኬኒያ ወንድም ህዝቦች ጋር መሆኑን አስረድተዋል።

በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡ መኮንኖች ቤተሰቦችና ወዳጆች በራሳቸውና በኢ.ፌ.ዲ.ሪ መከላከያ ሠራዊት ስም መጽናናትን ተመኝተዋል።

የኬንያ ጦር አዛዥ ጄኔራል ፍራንሲስ ኦሞንዲ ኦጎላ በምዕራብ የአገሪቱ ክፍል ይበሩበት የነበረው ወታደራዊ ሄሊኮፕተር ተከስክሶ ሕይወታቸው ማለፉን ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ትላንት ማሳወቃቸው ይታወሳል። ፕሬዝዳንቱ አደጋው ለአገሪቱ “ትልቅ ሐዘን” ነው ማለታቸውም ተገልጿል።