ፊቤላ ኢንዱስትሪ 12 ነጥብ 2 ሚሊየን ሊትር የሚጠጋ ዘይት አምርቶ ለገበያ አቅርቧል- አቶ በላይነህ ክንዴ

አቶ በላይነህ ክንዴ

ሚያዝያ 04/2013 (ዋልታ) – ፊቤላ ኢንዱስትሪ በመጀመሪያው ዙር የውጭ ምንዛሪ ተመድቦለት ባስገባው ጥሬ እቃ ተጠቅሞ 12 ነጥብ 2 ሚሊየን ሊትር የሚጠጋ ዘይት እና 1 ነጥብ 8 ሚሊየን ተጓዳኝ ምርቶችን አምርቶ ለገበያ ማቅረቡን የፊቤላ ኢንዱስትሪ ባለቤትና የቢኬጂ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ በላይነህ ክንዴ አስታወቁ።

ስምንት ሚሊየን የሚጠጋውን በአከፋፋዮች አማካኝነት ለህዝብ ማድረሱን የጠቆሙት አቶ በላይነህ ክንዴ፣ የተቀረው በመጫን ላይ ይገኛል ብለዋል።

ከአከፋፋዮች ቁጥር ማነስ ጋር በተያያዘ ምርቶችን ለተጠቃሚው የማዳረስ ችግር ተከስቶ እንደነበር ያመለከቱት አቶ በላይነህ፣ ችግሩን ከግምት ውስጥ በማስገባት መንግሥት በሃገር አቀፍ ደረጃ 33 አከፋፋዮች ወደዚህ ሥራ ማስገባቱንና ከእነዚህም ውስጥ ሰባቱ ለድርጅታቸው የተመደቡ በመሆኑ የስርጭት ችግሩ ሙሉ ለሙሉ ይቀረፋል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል።

ድርጅታቸው በመጀመሪያው ዙር በተፈቀደለት ውጭ ምንዛሪ 14 ሚሊየን ሊትር ድፍድፍ ዘይት ከውጪ አስገብቶ እንደነበር ያስታወሱት አቶ በላይነህ፣ በሁለተኛው ዙር ደግሞ 20 ሚሊየን ሊትር ድፍድፍ ዘይትና ሌሎች የማሸጊያ እቃዎች ከማሌዥያ አዞ ጅቡቲ ደርሶ በመጓጓዝ ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

እስከአሁን የፋብሪካው የዘይት ምርቶች በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ክልል፣ በአማራ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ እና በጋምቤላ ክልሎች እየተሰራጩ መሆኑን የጠቆሙት አቶ በላይነህ፣ ለአካባቢዎቹ የተመደቡ አከፋፋዮች ምርት እየወሰዱ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ስርጭቱን በተመለከተ ከመንግሥት ጋር በቅርበት እየሠሩ እንደሚገኝና ለዚህም መንግሥት ሊመሰገን እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

መንግሥት ለዘይት ቅድሚያ በመስጠት ካለችው የውጭ ምንዛሪ ለዚህ ሥራ መመደቡ ትልቅ ድጋፍ ነው የሚሉት አቶ በላይነህ፣ እኛም የተሰጠንን የተሻለ ዕድል በአግባቡ በመጠቀም ምርታችንን ለህዝቡ እያቀረብን እንገኛለን ብለዋል።

ምርትን በኃላፊነት ማሰራጨት በራሱ ከባድ ሥራ ነው ያሉት አቶ በላይነህ፣ ይህንን ሥራ መስመር ለማስያዝ ጥቂት መንገራገጭ ሊኖር እንደሚችልና በሚቀጥሉት 15 እና 20 ቀናት ውስጥ እነዚህ ሁሉ አከፋፋዮች ወደ ሥራ ሲገቡ ኅብረተሰቡ በበቂ ሁኔታ ምርቱን ሊያገኝ እንደሚችል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ፊቤላ እስካሁን ድረስ አንድ ሊትር ከ39.05 እስከ 42 ብር ለአከፋፋዮች እያቀረበ እንደሚገኝ ያስታወቁት አቶ በላይነህ፤ ይህ ዋጋ በዓለም ላይ አንድ ሊትር ዘይት ከሚሸጥበት ዋጋ በእጅጉ ያነሰ እንደሆነ ጠቁመዋል። በማሌዥያም ሆነ በሌሎች አገራት የአንድ ሊትር ዘይት ዋጋ ከአንድ ዶላር በላይ እንደሆነ መግለፃቸወን ኢፕድ ዘግቧል።