ፍርድ ቤቱ 10 ቦምቦችን በቤት ውስጥ ደብቀው ተይዘዋል በተባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ ለተጨማሪ ምርመራ የ12 ቀን ጊዜ ፈቀደ

ሚያዝያ 25/2015 (ዋልታ) በአዲስ አበባ የሽብር ወንጀል ለመፈፀም በማሰብ 10 ቦምቦችን በቤት ውስጥ ደብቀው ተይዘዋል በተባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ ፍርድ ቤቱ ለተጨማሪ ምርመራ የ12 ቀን ጊዜ ፈቀደ።

ህገመንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለማፍረስ በኢ-መደበኛ አደረጃጀት ተደራጅተው በአዲስ አበባ ከተማ የሽብር ወንጀል ለመፈፀም በማሰብ ከአማራ ክልል 10 ቦምቦችን በማምጣት በየካ ክፍለ ከተማ በተከራዩበት መኖሪያ ቤት ውስጥ ቦምቦችን ደብቀው ተይዘዋል በተባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ ነው ተጨማሪ ምርመራ እንዲደረግባቸው ነው ለፖሊስ የ12 ቀን ጊዜ የተፈቀደው።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን መርማሪ በአዲስ አበባ ከተማ ሁከትና ብጥብጥ በማስነሳት፣ የሽብር ወንጀል ለመፈፀም በማሰብ በተከራዩበት መኖሪያ ቤት 10 ቦንቦችን ደብቀው የተያዙ ሞላልኝ ሲሳይ እና አብርሃም ጌትነት በተባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ ከዚህ በፊት በተሰጠው የምርመራ ጊዜ ውስጥ የምስክሮችን ቃል መቀበሉ እንዲሁም ከተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊት ጋር የተያያዙ በርካታ ማስረጃዎች መሰብሰቡን የተጠርጣሪዎችንም ቃል መቀበሉን ለችሎቱ አስረድቷል።

በሁለተኛው መዝገብ ደግሞ ማለትም በአማራ ክልል አመፅ፣ ሁከትና ብጥብጥ በማስነሳት በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስ በማድረግ፣ አንዱ ህዝብ በአንዱ ህዝብ ላይ መተማመን እንዳይኖረው ለመከፋፈል ሲሰሩ ነበሩ ተብለው የተጠረጠሩ ሰይፈ ተስፋዬ፣ ማስረሻ እንየው፣ ጌታቸው ወርቄ፣ አንደበት ተሻገር፣ ታደሰ ወዳይነው በተባሉ 5 ተጠርጣሪዎች ላይ ከዚህ በፊት በተሰጠው ጊዜ ቀጠሮ የሰራውን የምርመራ ስራ ለችሎቱ አቅርቧል።

መርማሪ ፖሊስ በሁለቱም መዝገቦች ቀሪ ስራዎችን አከናውኖ የምርመራ ማጣሪያ አድርጎ ለመቅረብ ተጨማሪ የ14 ቀን ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቆ ነበር።

በሁለቱም መዝገብ የተሰየሙ የተጠርጣሪ ጠበቆችም ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ መፈቀድ የለበትም በማለት ተከራክረው ለተጠርጣሪዎች የዋስትና መብት እንዲፈቀድ ጠይቀዋል፡፡

መርማሪ ፖሊስ የተጠርጣሪዎች የዋስትና ጥያቄን በመቃወም ተከራክሯል።

በዚህም መሰረት የተጠርጣሪዎችን ዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ሞላልኝ ሲሳይ እና አብርሃም ጌትነትን በሚመለከት ተጨማሪ ምርመራ እንዲደረግ ፍርድ ቤቱ ለፖሊስ የ12 ቀን ጊዜ ፈቅዷል።

እነሰይፈ ተስፋዬ 5 ተጠርጣሪዎችን በሚመለከት ፍርድ ቤቱ የ10 ቀናት ተጨማሪ ጊዜን ለፖሊስ ፈቅዷል።

በዚሁ መዝገብ ተካተው የነበሩ ታደለ መንግስቱና አሰፋ አዳነ (ዶ/ር) የተባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ ተጨማሪ ጊዜ መሰጠት አስፈላጊ አይደለም ሲል ፍርድ ቤቱ እያንዳንዳቸው በ15 ሺሕ ብር ዋስ አስይዘው ከእስር እንዲፈቱ አዟል።

በሳሙኤል ሓጎስ