በሀረሪ ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ1 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ

ሚያዝያ 25/2015 (ዋልታ) በሀረሪ ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ1 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ በቀለ ተመስገን በክልሉ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት 1 ቢሊየን 131 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 1 ቢሊየን 179 ሚሊየን ብር የሚጠጋ ገቢ መሰብሰቡን ገልጸዋል።

ገቢው የተሰበሰበው ከቀጥታ ታክስ፣ ቀጥታ ካልሆነ የታክስ፣ ታክስ ነክ ካልሆኑ ገቢዎች እና ከማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ ገቢዎች መሆኑን አብራርተዋል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተሰበሰበው ገቢም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ364 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ጭማሪ እንዳለው ጠቁመዋል።

በክልሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚሰበሰበው ገቢ እያደገ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይም ገቢን አሟጦ ከመሰብሰብ አንፃር እየተሰሩ የሚገኙ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላል ብለዋል።

ክልሉ በ2015 የበጀት ዓመት 1 ነጥብ 36 ቢሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱም ተጠቁሟል።

ተስፋዬ ኃይሉ (ከሀረር ቅርንጫፍ)