ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ሴት የዩንቨርሲቲ ተማሪዎችን ስኬታማ የማድረግ መርሀግብርን አስጀመሩ

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አዲስ ገቢ የዩንቨርሲቲ ሴት ተማሪዎችን ለማብቃትና ስኬታማ የማድረግ መርሀግብርን ዘሬ አስጀምረዋል።

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ስርአተ ጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥ መንግስት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰው ሴቶችን በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ዘርፎች ተጠቃሚነታቸውን የማረጋገጥ ብሎም ወደ አመራር ለማምጣት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

በመርሀ ግብሩ የዩንቨርሲቲ አዲስ ገቢ ሴት ተማሪዎችን ስኬታማ  ከሆኑ ሴቶች ጋር በማጣመር ለሀገር የሚጠቅሙ ሴቶችን ለማብቃት፣ በተመደቡበት ዩንቨርሲቲ የሚገጥሙአቸዉን ችግሮች በመጋራትና በማገዝ ውጤታማነታቸውን ለማረጋገጥ እንደተዘጋጀ ታውቋል።

ተምሳሌት መሆን የምትችል ስኬታማ ሴት የትምህርት፣ የስራ፣ የህይወት ተሞክሮዎችን በማካፈል የዛሬ ለጋ ወጣት ሴት የነገዋ ኢትዮጵያ የስኬት ቁንጮን ለማብቃት የተዘጋጀ የምክክር መርሀግብር መሆኑም ነው ተብሏል።

መርሀግብሩ በ50 ተማሪዎች የተጀመረ ሲሆን ተደራሽነቱን በማስፋት ሴቶችንና ወንዶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታስቧል።

(በሃኒ አበበ)