ኮሚሽኑ በአምስት ወራት ለ20,357 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን አስታወቀ

የኦሮሚያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በአምስት ወራት ብቻ ለ20 ሺህ 357 ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር መቻሉን አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ በአጠቃላይ ለ634 ሺህ 500 በላይ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር መቻሉን ዛሬ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ተመልክቷል፡፡

የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ባዩሻ በዳዳ በመግለጫው እንዳብራሩት ኮሚሽኑ በ2012 ተሻሽሎ በወጣው የክልሉ የኢንቨስትመንት ደንብ መሰረት ወደ ተግባር ገብቷል፡፡

የአገልግሎት አሰጣጥ ብቃትና ጥራት ለማረጋገጥ በስምንት ከተሞች እና በሁለት ዞኖች የአንድ መስኮት አገልግሎት መስጠት ተጀምሯል፡፡

በዚህም በሃገር ውስጥም ሆነ ከሃገር ውጭ የሚገኙ ባለሃብቶች ጉዳዩን ለማስፈጸም ከአንድ ተቋም ወደ ሌላ የሚዘዋወሩበትን ድካም በመቀነስ እና መረጃን በቀላሉ የሚያገኙበት እና ጥያቄ የሚጠይቁበት ‘ኦሮሚያ ኢንቨስትመንት ዳትኮም’ የተሰኘ ፕላትፎርም ተዘጋጅቷል፡፡

ባለፉት አምስት ወራት በተለያዩ ምክንያቶች የቆሙ 79 ፕሮጀክቶች ወደ ስራ እንዲገቡ ሲደረግ 83ቱ ደግሞ በተደረገላቸው ድጋፍ ወደ ማምረት መግባታቸውን ዶ/ር ባዩሻ ገልጸዋል፡፡

በውሉ መሰረት መስራት ያልቻሉ 18 ፕሮጅክቶች የጹሑፍ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ሲሆን 62 ፕሮጀክቶች ደግሞ ውላቸው ተሰርዟል፡፡

(በነስረዲን  ኑሩ)