ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ የሀሳብ ልዩነቶችን ለመቅረፍ ከምክክር የተሻለ መፍትሄ አለመኖሩን ገለጹ

ሚያዝያ 19/2016 (አዲስ ዋልታ) በሀገራችን እየተስተዋሉ ያሉትን የሀሳብ ልዩነቶችንና ግጭቶችን እንዲሁም የቆዩና ስር የሰደዱ ችግሮችን ለመቅረፍ ከምክክር ባሻገር የተሻለ መፍትሄ አለመኖሩን የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።

ፕሬዝዳንቷ ይህን የገለጹት ኮሚሽኑ በሀገራዊ ምክክር ዙሪያ የሴቶች ተሳትፎን በተመለከተ እያካሄደ በሚገኘው የምክክር መድረክ ላይ ነው።

ሀገራዊ ምክክሩ ግጭቶችንና አለመግባባቶችን ለመፍታት ጉልህ ሚና ያለው መሆኑን የጠቆሙት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ይህንንም በርካታ የዓለም ሀገራት ተግባራዊ አድርገው እንደተሳካላቸው አንስተዋል።

በዚህ በኢትዮጵያ የቆዩና ስር የሰደዱ ችግሮችን ለመቅረፍ እየተተገበረ በሚገኘው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ውስጥ ሴቶች በንቃትና በብቃት መሳተፍ እንደሚገባቸው ገልጸው ለስኬቱ ሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች በባለቤትነት መንፈስ ሊሳተፉበት ይገባል ብለዋል።

በምክክር ሂደቱ ላይ መሳተፍ ካለባቸውና ጨርሰው ሊዘነጉ ከማይገቡ የማህበረሰብ ክፍሎች መካከል ሴቶች ዋነኞቹ መሆናቸውን አንስተው ይህም ትብብር ሳይሆን መብታቸው መሆኑን ገልፀዋል።

በችግሮችና በግጭቶች ወቅት ቀዳሚ ተጠቂ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውን በማንሳትም በመፍትሄ ሂደቱ ውስጥ ሚናቸው የጎላ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
ስለ ሰላምና አድገት እያሰቡ ሴቶችን አለማሳተፍ አይቻልም፤ እቅዱም አይሳካም የሚሉት ደሞ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ናቸው።

የሀገሪቱ ሴቶችም ይህን በመረዳት የነቃ ተሳትፎ ለማድረግ መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

የምክክር ኮሚሽኑ ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) በበኩላቸው ኮሚሽኑ አካታችና አሳታፊ ምክክር ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ማከናወኑን ጠቅሰው በዚህ ሂደትም ሴቶች ተሳታፊ እንዲሆኑ ተደርጓ ብለዋል።

ከኮታና ቁጥር በዘለለ በሀሳብም ተሳታፊ እንዲሆኑ በመደረጉ ሂደቱን ተስፋ ሰጪና ሙሉ ያደርገዋል ሲሉም አክለዋል።

በታምራት ደለሊ