አስቸኳይ እርዳታ ለሚሹ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገለጸ

አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር)

ሚያዝያ 19/2016 (አዲስ ዋልታ) አስቸኳይ እርዳታ ለሚሹ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) ገለጹ።

ኮሚሽነሩ በተለያዩ አካባቢዎች እየተከናወነ ያለውን የሰብአዊ ድጋፍና ተደራሽነትን በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ በሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የዓይነትና የገንዘብ ድጋፍ በተጠናከረ መልኩ እየቀረበ መሆኑን ገልጸዋል።

የሰብአዊ ድጋፉ በየሩብ ዓመቱ እንደሚሰራጭ ጠቅሰው ከጥር እስከ መጋቢት ድረስ ለ6 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዜጎች ድጋፍ ሲደረግ መቆየቱን ጠቁመዋል።

አሁን ባለንበት ወቅትም ከሚያዝያ እስከ ሰኔ ከስምንት ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሰብአዊ ድጋፍ ተደራሽ የማድረጉ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ድጋፉ በመንግስትና በአጋር አካላት ትብብር እንደሚከናወን የገለጹት ኮሚሽነሩ በአጠቃላይ ከሚያዝያ እስከ ሰኔ ላለው ድጋፍ 11 ቢሊዮን ብር አካባቢ ወጭ እንደምጠይቅና 5 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ ድጋፍ በመንግስት ይሸፈናል ብለዋል፡፡ ቀሪው በለጋሽ አካላት እንደሚሸፈንም ነው የተናገሩት፡፡

የመንግስት ዋነኛ ትኩረት አደጋን ቀድሞ መከላከል መሆኑን የተናገሩት አምባሳደር ሽፈራው ለዚህም የተጋላጭነት ልየታ የአደጋ ስጋት ፕሮፋይል ጥናት መሰራቱን ጠቁመዋል።

በሀገሪቱ ከሚገኙ ወረዳዎች ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በዚህ ጥናት መሸፈናቸውንም ተናግረዋል።