ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር በአባይ ወንዝ ገባሮች ላይ የሚካሄዱ ቁፋሮዎች እንዲቆሙ አዘዙ

ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት

ሐምሌ 6/2014 (ዋልታ)  በአባይ ወንዝ ገባሮች ላይ የሚካሄዱ ቁፋሮዎች እንዲቆሙ አዘዙ።

“የጆንግሌይ ካናል” በደቡብ ሱዳን የሚገኘውን የሱድ ረግረጋማ አካባቢ በማድረቅ ለግብርና አገልግሎት እንዲውል በማድረግ ብዙ ውሃ ወደ ሱዳን እና ግብፅ ለማስተላለፍ የተጀመረ ነገር ግን ያልተጠናቀቀ የቦይ ፕሮጀክት ነው።

“የጆንግሌይ ካናል” ፕሮጀክትን ወጪ የሸፈነችው ግብፅ ከዚህ ረግረጋማ አካባቢ የሚወጣውን ትነት በመቀነስ የውሃውን ፍሰት ካይሮ ለማድረስ የሚያስችል የገንዘብ ድጋፍ ያደረገች ሲሆን የደቡብ ሱዳን መንግሥት መነሻቸውን ከግብፅ ያደረጉ 21 ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎችን በሱዳን በኩል ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚያስገባም ገልፆ ነበር።

ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎቹ የአባይ ወንዝ ገባሮችን ከአረም እና ከጭቃ ለማፅዳት የሚጠቀምባቸውን ማሽኖች ጭነው ከግብፅ እንደሚመጡ መገለፁም ይታወቃል።

በዚህም እንደ ኤድመንድ ያካኒ ያሉ የደቡብ ሱዳን ታዋቂ የመብት ተሟጋች የፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት መንግሥት የሱድ ረግረጋማ ቦታዎችን በማድረቅና ሰው ሰራሽ ወንዞችን በመቀየስ “የጆንግሌይ ካናል” ግንባታ ለማስቀጠል ሥራ መጀመሩን ተቃውመዋል።

እቅዱን በተመለከተ ታማኝ እና ገለልተኛ በሆኑ አካላት ጥናቶች መደረግ እንዳለበት በማስገንዘብ አገሪቱን ለግብፅ ጥቅም “መሸጥ” እንደማይገባ ሲያሳስቡም እንደነበር የዘ ኢስት አፍሪካ ዘገባ አስታውሷል።

የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት ከግብፅ ጋር በተደረገው ስምምነት መንግሥታቸው ላይ በአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች እና በመብት ተሟጋቾች ተቃውሞ መነሳቱን ተከትሎ በአባይ ወንዝ ገባሮች ላይ የሚካሄዱ ማናቸውንም ቁፋሮዎች እንዲቆሙ አዘዋል።

ፕሬዝዳንቱ የጆንግሌይ ቦይ ፕሮጀክት እንደገና ከመጀመሩ በፊት ፕሮጀክቱ በማኅበረሰቡ እና በሥነ-ምህዳር ላይ ስላለው ተጽእኖ የአካባቢ ጥናቶች መደረግ እንዳለበት ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

የፕሬዘዳንቱ ውሳኔ ከአንድ ዓመት በላይ የዘለቀውን ሕዝባዊ ክርክር እንዲቆም ያደረገ ሲሆን በጉዳዩ ዙሪያ ከግብፅ ወገን የተባለ ነገር እንደሌለም ዘገባው አመላክቷል።

በደረሰ አማረ