ፖሊስ 278 ኪሎ ግራም የሚመዝን አደንዛዥ እጽ በቁጥጥር ሥር አዋለ

በምዕራብ ጉጂ ዞን የአባያ ወረዳ ፖሊስ በተሽከርካሪ ተጭኖ ወደ ሞያሌ ሲጓጓዝ የነበረ 278 ኪሎ ግራም የሚመዝን አደንዛዥ እጽ በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታወቀ።

የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ሻምበል ደረሰ ለኢዜአ እንዳሉት፤ አደንዛዥ እጹ በቁጥጥር ሥር የዋለው ከሀዋሳ ወደ ኬንያ ሞያሌ ከተማ እየተጓጓዘ በምዕራብ ጉጂ ዞን አባያ ወረዳ ሰመሮ ቀበሌ ሲደርስ ነው፡፡

ፖሊስ አደንዛዥ እጹን ሲጓጓዝበት ከነበረው ተሽከርካሪ ጋር ጥር 11 ቀን 2013 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እያደረገ ሲሆን፤ እጹን በማዘዋወር የተጠረጠረውን ግለሰብ ፖሊስ ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን ለመቆጣጠር ክትትል እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በህዝብ ጥቆማ በቁጥጥር ሥር የዋለው አደንዛዥ እጽ ከአንድ ሚሊየን ብር በላይ እንደሚገመት ያመለከቱት የፖሊስ አዛዡ፤ የእጹን ዓይነት ለመለየት ለፌዴራል ፖሊስ ፎረንሲክ ምርመራ እንደሚላክ ገልጸዋል።

የወረዳው ዋና አስተዳደር አቶ አያኖ አለማየሁ በበኩላቸው ህገ ወጥ እንቅስቃሴን ለመከላከል ከግለሰብ እስከ መንግስት ተሽከርካሪዎች የተጠናከረ ፍተሻና ቁጥጥር በመደረግ ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

ህገ ወጥነትን ለማስቀረት የተለያዩ አካላትን ያካተተ ኮሚቴ መቋቋሙንም ተናግረዋል፡፡

የአካባቢው ህብረተሰብ ህገ ወጥ እንቅስቃሴን በማጋለጥ ረገድ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ በመቀጠል ከወረዳው ባለድርሻ አካላት ጋር ተባብሮ እንዲሰራ ጠይቀዋል፡፡

በምዕራብ ጉጂ ዞን ባለፉት ስድስት ወራት 22 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው አደንዛዥ እጽና የኮንትሮባንድ እቃዎች በቁጥጥር ሥር ማዋል መቻሉን የዞኑ ፖሊስ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ዲቪዥን ሀላፊ ዋና ሳጂን ፈዬራ ከይረዲን ገልጸዋል።