2ኛው ሀገር አቀፍ የሞዴል ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ባዛር ተከፈተ

ሚያዚያ 18/2013 (ዋልታ) – 2ኛው ሀገር አቀፍ የፌዴራል የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ከአዲስ አበባ የሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ጋር በጋራ ያዘጋጁት ባዛር ተከፈተ፡፡

ባዛሩ ለሞዴል የጥቃቅንና አነስተኛ አንቀሳቃሾች ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅና የገበያ ትስስር ለመፍጠር እንደሚያስችል ተገልጿል፡፡

ባዛሩን የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር አይሻ መሃመድ ከአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጋር በመሆን በጋራ ከፍተውታል፡፡

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሯ አይሻ መሃመድ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ሀገሪቱ የምታደርገውን የልማት ጉዞ ከማስቀጠል አንፃር ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው አንስተዋል፡፡ በመሆኑም መንግስት ዘላቂና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ድጋፉን ያደርጋል ነው ያሉት፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው ኢንተርፕራይዞቹ ከጊዜያዊ ትርፍ በላይ ዘላቂ የገበያ ትስስር በመፍጠር ራሳቸውን በማሳደግና የኑሮ ውድነትን በማቃለል ያላቸውን ከፍተኛ ድርሻ እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ጀሞ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የገበያ ማዕከል የተከፈተው ባዛር ለ7 ቀናት እንደሚቆይ ተገልጿል፡፡

(ሳሙኤል ሀጎስ)