በክልሉ የሰብል በሽታ ጉዳት ሳያደርስ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ተቻለ

በአማራ ክልል በተለያዩ ሰብሎች ላይ የተከሰቱ በሽታዎች ጉዳት ሳያደርሱ ለመከላከልና ለመቆጣጠር መቻሉን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡  

በክልሉ ቢጫ ዋግ፣የግሪሳ ወፍ፣አገዳ ቆርቁርና አንበጣን የመሳሰሉ የሰብል በሽታዎች በተወሰኑ አካባቢዎች ቢከሰቱም ጉዳትና ተፅዕኖ ሳያደርሱ በቁጥጥር መዋላቸው ነው የተመለከተው፡፡

ቢሮው በሽታዎቹን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወሰደው አፋጣኝ እርምጃ ችግሩ ስር ሳይሰድ ሊከሽፍ መቻሉን በቢሮው የሠብል ልማትና ጥበቃ ቴክኖሎጂ ማስፋፊያ የስራ ሂደት አስተባባሪ ዶክተር ሽመላሽ የሻነህ ለዋልታ ገልፀዋል፡፡

አረምና ተባይን በማጥፋት አቅሙ ተመራጭ የሆነውን የተቀናጀ የተባይ መከላከያ ኬሚካል በሽታዎቹ በተከሰቱባቸው አካባቢዎች እንዲረጭ ተደርጓል፡፡ በባህላዊ መንገድ ተባዮችን መከላከል ዋናው ተመራጭ ስልት መሆኑን ዶክተር ሽመላሽ ይናገራሉ፡፡

በዚህም መሰረት አርሶ አደሩ አረምን በመንቀልና ማሳን በመንከባከብ በሽታን የመከላከል ሥራ እንዲያከናውን ግንዛቤ የማስጨበጥና የመደገፍ ሥራ ተሰርቷል፡፡ በተወሰኑ ዞኖች ተከስቶ የነበረው የስንዴ ዋግ በኬሚካል ርጭት እንዲወገድ መደረጉን አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡

‹‹ስንዴ ሲዘራ የዋግ በሽታ ሊከሰት እንደሚችል ይጠበቃል›› ያሉት ዶክተር ሽመላሽ ስንዴ አምራች በሆኑ የክልሉ የተለያዩ ዞኖች በሽታው መከሰቱን አስረድተዋል፡፡ በሽታው በምስራቅ ጎጃም፣ በደቡብና ሰሜን ወሎ፣ በደቡብ ጎንደር አካባቢ መከሰቱን ተፅዕኖና ጉዳት ሳያደርስ በቁጥጥር መዋሉን አስገንዝበዋል፡፡

በሰሜን ሸዋ ዞን የተከሰተው የግሪሳ ወፍም ጉዳት እንዳያደርስ በአውሮፕላን የኬሚካል ርጭት እየተደረገ ነው፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተውን አንበጣ ለመከላከል በባህላዊና በአውሮፕላን የኬሚካል ርጭት ተካሂዷል፡፡ የደረሱ ሰብሎች ላይ ኬሚካሉ እንዳይረጭ እንዲሰበሰቡ ተደርጓል፡፡ በቆሎን የሚጠቃውን የአገዳ ቆርቁር ተባይንም በፀረ ተባይ ኬሚካል የመከላከል ሥራ ተሰርቷል፡፡

ዶክተር ሽመላሽ እንዳሉት ባለፈው ዓመት ለኬሚካል መግዥያ 10 ሚሊዮን ብር ተመድቦ ግዥ ተፈፅሟል፡፡ ይህም በወቅቱ ሙሉ በሙሉ ጥቅም ላይ ሳይውል በመትረፉ አሁን ችግር በተከሰተባቸው አካባቢዎች ተከፋፍሎ እንዲረጭ ተደርጓል፡፡

በተያዘው ዓመት በክልል ደረጃ 13ሺ ሊትር ተጠይቆ በየጊዜው እየተለቀቀ ሲሆን ከፌዴራልም 4ሺ ሊትር ኬሚካል መጠየቁን አስተባባሪው አስረድተዋል፡፡ ‹‹የኬሚካል እጥረት አላጋጠመም፤ ሥራውም ከአቅም በላይ አልሆነም›› ብለዋል፡፡