መንግሥት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዙሪያ ለዲያስፖራዎች ገለጻ ሊያደርግ ነው

መንግሥት በአገሪቱ ተግባራዊ እየተደረገ ስላለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመጪው ረቡዕ ገለጻ እንደሚያደርግ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበር አስታወቀ ።   

የማህበሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አብርሃም ስዩም በሠጡት መግለጫ  እንደገለጹት ማህበሩ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ልክ እንደ አንድ የአገሪቱ ዜጋ በአገራቸው የፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ፎረም አዘጋጅቷል ።

በፎረሙ 1ሺ የሚገመቱ የዲያስፖራ አባላት ይሳተፋሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን የተለያዩ  የመንግሥት  የሥራ ኃላፊዎች  በተገኙበት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን  ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ  ወቅታዊ  ሁኔታዎች ላይ ከዳያስፖራ  አባላት ጋር ውይይት ይካሄዳል ።                

እንደ አቶ አብርሃም ገለጻ የዳያስፖራ አባላት በአገሪቱ ወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮች እንደ  ዜጋ የሚመለከታቸው በመሆኑ በአገሪቱ በሚካሄዱት ሁሉ አቀፍ የመፍትሄ እርምጃ  አንድ አካል በመሆን የመሳተፍ ፍላጎት አላቸው ብለዋል ።       

የተለያዩ  የመንግሥት ባለሥልጣናት  ረቡዕ በሚደረገው ፎረም ላይ  በመገኘት  በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አተገባበር ዙሪያ  ከተለያዩ አገራት ለሚመጡና በአገር ውስጥ ለሚገኙ የዲያስፖራ አባላት  ገለጻ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል ።

የዲያስፖራ  አባላቱ በወቅታዊ የአገሪቱ  የፖለቲካ ጉዳዮችን  በማስመልከት ያሏቸውን ጥያቄዎች ለመንግሥት ሥራ ኃላፊዎቹ እንዲያቀርቡ እድል የሚፈጥር መሆኑም አቶ አብርሃም አመልክተዋል ።

የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አባላት ለአገሪቱ  የሰላም፣ልማትና የዴሞክራሲ ዕድገት የሚኖራቸው አስተዋጽኦ የላቀ መሆኑን የጠቆሙት  አቶ አብርሃም  በቅርቡ በአንዳንድ የአገሪቱ  አካባቢዎች  በተከሰቱት  ሁከቶች  ምክንያት የንብረት ውድመት ስለደረሰባቸው የዲያስፖራ አባላትና ስለ የፌደራሊዝም ሥርዓቱ በፎረሙ ወይይት  ከሚደረግባቸው አጀንዳዎች መካከል ይገኛሉ ።           

በተጨማሪም  የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አባላት  በአገሪቱ  ፖላቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች  ላይ ምን አይነት ሚና መጫወት እንደሚችሉ  የሚያሳይ ጥናታዊ ጽሑፎች እንደሚቀርብ ተጠቁሟል ።

የዓለም ባንክ ያወጣው መረጃ  እንደሚያመለክተው  ከ 2 ሚሊዮን በላይ  የሚሆኑ የኢትዮጵያ ዲያስፖራዎች  በተለያዩ  ዓለማት ይኖራሉ ።