እህትማማች ከተሞች የድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ

ልዩ ድጋፍ የሚሹ ክልሎች ከተሞች ልማታቸውን ለማጠናከር ከአራቱ ዋና ዋና ክልል ከተሞች ጋር የእህትማማች ከተሞች የድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

አዳማ ከጅግጅጋ፣ መቀሌ ከሰመራ፣ ሀዋሳ ከጋምቤላ፣ እንዲሁም ባህር ዳር ከአሶሳ ከተማ ጋር በትብብር ለመስራት የድጋፍ ስምምነቱን ተፈራመዋል፡፡

ከተሞቹ በጅግጅጋ ከተማ የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ባካሄደው 12ኛው ዙር የከተሞችና ሴክተር መስሪያ ቤቶች ጉባዔ ላይ ነው ስምምነቱን የተፈራረሙት፡፡

በጉባዔው ከዘጠኙ ክልሎችና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን በተለይም ልዩ ድጋፍ በሚሹ ክልሎች ያለው አፈፃፀም ተገምግሟል፡፡

ልዩ ድጋፍ በሚሹ ክልሎች ለከተማ ልማት ሥራዎች ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር ዶክተር አምባቸው መኮንን ተናግረዋል፡፡

በየከተሞቹ የሚፈለገውን ልማት ለማስመዝገብና የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አመራ በቁርጠኝነት ሊንቀሳቀስ እንደሚገባ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል፡፡

አራቱ በልማት የተሸለ ደረጃ ላይ የደረሱት ኦሮሚያ፣አማራ፣ትግራይና የደቡብ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች ልዩ ድጋ ለሚሹ ክልሎች ከተሞች የሚያደርጉት ድጋፍና የተሞክሮ ለውውጥ አነስተኛ መሆኑ በጉባዔው ተገምግሟል፡፡

የእህትማማች ከተሞች የድጋፍ ስምምነት በከተሞች መካከል የተጠናከረ ድጋፍና ትብብር እንዲኖር ለማድረግ እንደሚረዳ የተናሩት ደግሞ የከተማ ልማና ቤቶች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ደምሴ ሽቶ ናቸው፡፡

ልዩ ድጋፍ በሚሹ ክልል ከተሞች መካከል በተደረገው ግምገማ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የከተማ ልማት ሥራ ግንባር ቀደም ሆኗል፡፡ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከተማ ልማት ዘርፍ የተሻለ አፈፃፀም ማስመዝገቡ ተመልክቷል፡፡

የጋምቤላና የአፋ ክልሎች የከተማ ልማት አስተዳደር የከተማ ልማት ዘርፍ ወደ ኋላ የቀሩ መሆናቸው በግምገማው ተጠቅሷል፡፡    

ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈፃፀምና የዕቅዱ ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች ላይም ውይይትና ምክክር ተደርጓል፡፡

በከተሞች መኖሪያ ቤት ግንባታ፣ በመሬት ልማትና ማኔጅመንት ሥራ፣ በከተሞች የመልካም አስተዳደር ፓኬጆች፣ በከተማ ፕላን ሥራዎች፣በከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና በምግብ ዋስትና ዙሪያ ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

የጉባዔው አባላት በጅግጅጋ ከተማ የተከናወኑ የልማት ሥራዎችን በመጎብኘት ጉባዔው ነገ ይጠናቀቃል፡፡