በሞዛምቢክ የነዳጅ ማጠራቀሚያ ፈንድቶ 73 ሰዎች ሞቱ

በምዕራብ ሞዛምቢክ የነዳጅ ማጠራቀሚያ ፈንድቶ በትንሹ 73 ሰዎች ሞቱ፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ከ108 በላይ ደግሞ መቁሰላቸውን ቢቢሲ የሀገሪቱን ባለስልጣናት ጠቅሶ በዘገባው አመለከተ፡፡

በማላዊ ደንበር አቅራቢያ ቴቴ ክፍለ ግዛት ካፊሪዛንጄ በሚባለው አካባቢ ለፈነዳው የነዳጅ ማጠራቀሚያ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ግልፅ አልተደረገም፡፡

ነዳጅ የጫነ ከባድ ተሽከርካሪ ሲያሽከረክር የነበረ አሽከርካሪ ለአካባቢው ነዋሪዎች ነዳጅ ለመሸጥ ባደረገው ሙከራ ችግሩ ሳይከስት እንዳልቀረ የሚናገሩ መኖራቸው በዘገባው ተመልክቷል፡፡

በአካባቢው የነበረ ተቀጣጣይ ነገር ለእሳቱ መንስዔ ሳይሆን እንዳልቀረ የሚናገሩም አልጠፉም፡፡

ህይወታቸው ያለፉ ሰዎችን አስከሬን በመለየት ለቤተሰቦቻቸው ተሰጥቶ የተቀበረ ሲሆን በአደጋው ምክንያት አስከሬናቸውን ለመለየት አዳጋች የሆኑትን በጅምላ እንዲቀበሩ ተደርጓል፡፡

የሟቾቹ ቁጥር ከዚህ ሊበልጥ እንደሚችል አስተያታቸውን ለቢቢቺ የሰጡ የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡