የ11ኛው ዓለም አቀፍ የማይዳሰሱ ቅርሶች ጉባኤ ዝግጅት ተጠናቀቀ

በአዲስ አበባ የሚካሄደው 11ኛው ዓለም አቀፍ የማይዳሰሱ ቅርሶች ጉባኤ ዝግጅት ሥራ መጠናቀቁን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ጉባኤው ከህዳር 19 እስከ 23 ቀን 2009 ዓ·ም እንደሚካሄድ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ወልደማርያም የጉባኤውን ዝግጅትን አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አመልክተዋል።

በዚህም ከውጭ ጉዳይ፣ ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት፣ ከፊደራል ፖሊስ፣ ከአዲስ አበባ ፖሊስ፣ ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የተውጣጣ ብሄራዊ ኮሚቴ እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅት ማድረጉን ተናግረዋል።

የጉባኤው መዘጋጀት ኢትዮጵያ ውሰጥ ያሉ የሚዳሰሱ፣ የማይዳሰሱ፣ ባህላዊና ተፈጥሯዊ ቅርሶችን ለቀሪው ዓለም ለማሳየት ምቹ ሁኔታ እንደሚኖረው ሚኒስትሯ ጠቁመዋል።

አገሪቱ የምታገኘውን የኮንፈረንስ ቱሪዝም ገቢም እንደሚያሳድግ ገልጸው በአገሪቱ የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያስገኘውን ሰላም ለማሳየት ጠቀሜታው የጎላ ነውም ብለዋል።

በጉባኤው የማይዳሰሱ የዓለም ቅርሶች ያሉበትን ወቅታዊ ሁኔታ መሰረት ያደረጉ ውይይቶች ይካሄዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የቅርስና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ደስታ በ11ኛው ዓለማቀፍ የማይዳሰሱ ቅርሶች ጉባኤ ላይ ከተለያዩ አገራት ለቀረቡ 37 የማይዳሰሱ ቅርሶች የይመዝገቡልን ጥያቄዎች ምላሽ ይሰጣል ብለዋል።

የይመዝገቡልን ጥያቄ ከቀረበላቸው 37 የማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል 19ኙ ጥያቄ የተነሳባቸው ሲሆን ጥያቄውን ያቀረቡ አገራት በጉባኤው ምላሽ ይሰጣሉ ተብሎም ይጠበቃል።

ኢትዮጵያም ጥንታዊውን የገዳ ስርአት በማይዳሰሱ ቅርሶች የይመዝገብልኝ ጥያቄ ማቅረቧን አስታውሰው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ከታየ በኋላ በጉባኤው ምላሽ ይሰጥበታል ብለዋል።

ዩኔስኮ የመስቀልንና ፍቼ ጫምባላላን ህዝባዊ በዓላት በዓለም አቀፍ የማይዳሰሱ ቅርስ  መዝገብ ማስፈሩ ይታወሳል።

ኢትዮጵያ እ·ኤ·አ በ2003 የወጣውን በዓለም አቀፍ ደረጃ የማይዳሰሱ ቅርሶች ስምምነት እ·ኤ·አ  በ2006 ሙሉ በሙሉ ተቀብላለች።    

ለ11ኛ ጊዜ በአዲስ አበባ በሚካሄደው በዚህ ጉባኤ ላይ  እስከ አንድ ሺ የሚደርሱ የውጭ አገራት ተሳታፊዎች እንደሚገኙ ይጠበቃል።

10ኛው ዓለም አቀፍ የማይዳሰሱ ቅርሶች ጉባኤ በናሚቢያ መካሄዱ ይታወሳል።