አመራሩ የህዝብን ጥቅም ለማስቀደም ያሉበትን ውስንነቶች እየፈተሸ ነው

ስልጣንን በአግባቡ ከመጠቀምና የህዝብን ጥቅም በማስጠበቅ ረገድ የነበሩባቸውን ውስንነቶች በአግባቡ እየፈተሹ መሆኑን የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ(ሕወሓት) መካከለኛ አመራር አባላት ገለፁ፡፡

አመራሮቹ የታዩባቸውን ክፍተቶች ለማስተካከል ራሳቸውን በጥልቅ መገምገማቸውንና የአገሪቷን የህዳሴ ጉዞ ለማስቀጠል ቁርጠኛ አቋም መያዛቸውን ተናግረዋል፡፡

የድርጅቱ መካከለኛ አመራር አባላት ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ መሰብሰቢያ አዳራሽ የጥልቅ ግምገማ በማካሄድ ላይ ይገኛሉ፡፡

ኢዜአ ያነጋገራቸው የድርጅቱ አመራሮች ለተለያዩ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች መንስኤ የሆኑ ጉዳዮችን በመፈተሸ ለለውጥ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

ይህን ችግር ለመፍታትም እያንዳንዱ የሕወኃት አባል ያሉበትን ችግሮች በጥልቅ በመፈተሽ ማንኛውም ስልጣን ለህዝብ ጥቅም ብቻ መጠቀም እንደሚገባው መግባባት ላይ ተደርሷል ብለዋል፡፡

አመራሮቹ የህዝብን ጥቅም በማስቀደም የአገሪቷን የልማት የሰላምና የዲሞክራሲ ጉዞ ለማስቀጠል በቁርጠኝነት ለመስራት መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል፡፡ በህዝብ የተሰጣቸውን ስልጣን ለህዝብ እርካታ ለማዋል መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

አቶ ደሳለኝ ገብረ ዮሀንስ ባላቸው ኃላፊነት ከመቼውም ጊዜ በላይ ህዝብን ለማገልገል መዘጋጀታቸውን ይናገራሉ፡፡

‹‹ባደረግናቸው ግምገማዎች ችግሮችን ተገንዝቤአለሁ፡፡ ከችግሮቹ የመውጫ መንገዶችንም ተረድቻለሁ፡፡ በዚሁ መሰረት በገባነው ቃል መሰረት የያዝነውን ኃላፊነት ለህዝብ ጥቅም ለማዋል በበኩሌ አስተዋፅኦ አደርጋለሁ ብዬ እተማመናለሁ›› ብለዋል፡፡

ወይዘሮ አፀደ ታመነ በበኩላቸው በጥልቅ ተሃድሶው እንደ አንድ የድርጅቱ አባል እስከ አሁን መወጣት የነበረባቸውን ሚና በጉባዔው በአግባቡ መረዳታቸውን ገልፀዋል፡፡

‹‹ለጥልቅ ተሃድሶው የዳረጉን ችግሮች ከመፍታት አኳያ ምን ሚና ይኖረኛል የሚለውን ተረድቻለሁ፡፡ በዝርዝር ወደ እያንዳንዳችን ሂስና ግለሂስ ስንገባ ደግሞ የራሴን እወስዳለሁ››ብለዋል፡፡

በጥልቅ ተሃድሶው ራሳቸውን የለውጥ አካል ለማድረግ መዘጋጀታቸውን የተናገሩት ደግሞ አቶ ግርማይ አስገዶም ናቸው፡፡

‹‹በመጀመሪያ ራስን በደንብ ማየት መቻል አለብኝ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ሌሎች ጓዶች ጋር የሚታዩ መሰረታዊ ችግሮችን በግልፅ መታገል ይገባል፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ራሴን የተሃድሶ አካልና መፍትሔ እንድሆን እፈልጋለሁ›› ብለዋል፡፡

የተሃድሶ ግምገማው ለውጥ እንዲያመጣ እንደ ግለሰብም እንደ ድርጅት አባልም ጠንካራ ተሳትፎ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን የሚናገሩት ደግሞ ኣቶ ፀጋዬ በየነ ናቸው፡፡

‹‹ለህዳሴ ጉዞው እንቅፋት የሚሆኑ ችግሮችን አውቆ ራስን ከጠባብነት በማራቅ የህዝብ ውግንናን ይዞ ቁርጠኛ ሆኖ ከመስራት አንፃር የሚታዩ ጉድለቶችን በግል ማስተካከል ይገባል፡፡ ለተሰለፍኩለት ዓላማ ደግሞ ቀን ከሌሊት መስራት አለብኝ፡፡ ከእኔ የሚፈለገውን ነገር ሙሉ በሙሉ መስራት መቻል አለብኝ፡፡ በተቻለ መጠን ተሃድሶው ተሃድሶ መሆን አለበት፡፡ ለውጥ ካላመጣ አስቸጋሪ ነው፡፡ ሁላችንንም ችግር ውስጥ ሊያስገባን ይችላል፡፡ እነዚህን ችግሮች በተቻለ መጠን እንደ ግለሰብም ማስወገድ አለብን ብዬ ነው የማስበው›› ብለዋል፡፡

የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት(ሕወሓት) መካከለኛ አመራሮች ግምገማ እስከ ነገ የሚቀጥል ሲሆን ከአንድ ሺ በላይ የድርጅቱ መካከለኛ አመራር አባላት በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡(ኢዜአ)