ኢትዮጵያ የኮሪያን ሞዴል በመከተል ፈጣን እድገት አስመዝግባለች-ጠቅላይ ሚኒስትሩ

ኢትዮጵያ የኮሪያን የዕድገት ሞዴል በመከተል ፈጣንና ተከታታይ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገቧን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለፁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኮሪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዩን ብዩንግ ሲን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

በውይይታቸውም ኮሪያ የተገበረችውን የእድገትና ለውጥ ፈለግ ኢትዮጵያም በመከተል ፈጣንና ተከታታይ እድገት ማስመዝገቧን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ለፈጣን ዕድገቷ ዘላቂነት በቀጣይ አስፈላጊ ልምዶችን ከኮሪያ መቅሰም እንደምትፈልግም ገልፀውላቸዋል።

ኢትዮጵያ ከኮሪያ በተለይም በሰው ሃብት ልማት፣በሳይንስና ቴክኖሎጂና በከተማ ልማት ያላትን ልምድ መውሰድ እንድምትፈልግም በውይይታቸው አንስተዋል።

የኮሪያ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች የሚያደርጉትን ተሳትፎ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የኮሪያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዩን ብዩንግ በበኩላቸው ኢትዮጵያ እያስመዘገበችው ያለው ፈጣንና ተከታታይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት ቀጣይነት እንዲኖረው ኮሪያ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ ኤክስፖርት መር ኢንዱስትሪ መከተሏ የኮርያን ባለሃብቶች ትኩረት እየሳበች መሆኑንም እንዲሁ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ተግባራዊ ለምታደርጋቸው የልማት ፕሮጀክቶች የመሰረተ ልማትና የሰው ሃይል ስልጠና እገዛ የምታደርግ መሆኑን ውይይቱን የተከታተሉት በኮሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሽፈራው ጃርሶ ገልጸዋል።

የደቡብ ኮሪያ ፕሬዚዳንት ፓርክ ጄንሄይ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።

በጉብኝታቸውም ከኢትዮጵያ ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር እንዲሁም በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ለመስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።(ኢዜአ)