በሐረር ከተማ የተገነባው ሁለ ገብ የባህል ማዕከል በይፋ ተመረቀ

በሀረሪ ክልል የሚከበረውን 11ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓልን ምክንያት በማድረግ የተገነባው ሁለ ገብ የባህል ማዕከል ዛሬ በይፋ ተመረቀ፡፡

በ250 ሚሊዮን ብር  የተገነባው የባህል ማዕከል በአንድ ግዜ ሁለት ሺ 100 ሰዎችን በወንበር ማስተናገድ እንደሚችል በምርቃቱ ላይ ተመልክቷል፡፡

የባህል ማዕከሉን የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሙራድ አብዱል ሃዲ፣የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ወልደ ማርያምና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ያለው አባተ መርቀዋል፡፡

ባህል ማዕከሉ ዋናውን የስብሰባ አዳራሽ ጨምሮ አምስት ንዑሳን ፕሮጀክቶች እንዳሉት ተመልክቷል፡፡ 400 ሰዎችን ማስተናገድ የሚችሉ መለስተኛ የስብሰባ አዳራሾችና ሙዚየም ፣ለቢሮ አገልግሎት የሚውሉ ባለአምስት ፎቅ ክፍሎች፣ መለስተኛ ሆቴል፣ የሀረሪን ብሔረሰብ ባህላዊ የቤት አሰራር የሚያሳይ ፕሮጀክት እና የኦሎምፒክን ደረጃ የጠበቀ የመዋኛ ገንዳ አለው፡፡

ማዕከሉ በ17 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን አምስት በሮች አሉት፡፡ ይህም የሀረር መገለጫ የሆነውን የጀጎል ግንብን የበር ብዛት መሰረት ያደረገ ነው ተብሏል፡፡ ማዕከሉ ለአካል ጉዳተኞችም በሚመች መልሉ ዲዛይን ተደርጎ መገንባቱ ነው የተገለፀው፡፡

ዘመናዊና ደረጃቸውን የጠበቁ የመብራትና የድምፅ አገልግሎት የሚሰጡ መሳሪያዎች ተገጥመውለታል፡፡ የባህል ማዕከሉ ለጨለንቆ ሰማዕታት መታሳቢያ እንዲሆንም ተወስኗል፡፡

የሀረሪ ክልል የተለያዩ የልማት ሥራዎችን በስፋት እያከናወነች እንደምትገኝ የክልሉ የቤቶችና የመንግስት ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልሃኪ አብዱልማላኪ ለዋልታ ተናግረዋል፡፡

የክልሉ መንግስት በዓሉ በድምቀት የሚከበርበትና አጠቃላይ ግንባታው 65 በመቶ የደረሰው ስታዲየምን ጨምሮ በአንድ ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር የመንገድና የተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን እየገነባ መሆኑን ኃላፊው ገልፀዋል፡፡

የፌዴራል መንግስት አንድ ቢሊዮን ብር ወጭ በማድረግ የሚያስገነባው ቴርሼሪ ሆስፒታል ለምስራቅ ኢትዮጵያ በሪፈራል ሆስፒታልነት   ያገለግላል፡፡ ሆሲፒታሉ በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ሥር እንደሚተዳደር ኃላፊው ጠቁመው አንድ ሺ መኝታዎች እንዳሉት አስረድተዋል፡፡

ሀረርን የቱሪዝም፣የንግድና የተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ቀጣና ለማድረግ በሚያስችል መልኩ የተለያዩ የልማት ሥራዎች በስፋት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተመልክቷል፡፡