የአዲስ አበባ የመንገድ ትራንስፖርት ቢሮ የአንበሳ አውቶቢስ አገልግሎትን በ20 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለማዘመን የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ አስታወቀ ።
ከዓለም ባንክ በተገኘ የ20 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ የአንበሳ አውቶቢስን የትራንስፖርት እንቅስቃሴና አስተዳደራዊ ሥራዎችን በማዘመን የአዲስ አበባ ከተማ ውጤታማ የሆነ የመንገድ ደህንነትን ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ ይገኛል ።
የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ምትኩ አስማረ ለዋልታ እንደገለጹት የአንበሳ አውቶቢስን ለማዘመን የሚካሄደው ፕሮጀክት በየጊዜው በአዲስ አበባ ከተማ እያደገ የመጣውን የትራንስፖርት አገልግሎት ፍላጎት ለማስተናገድ ያግዛል ብለዋል ።
የአንበሳ አውቶቢስን የመዘመን ሥራው ሲጠናቀቅ በኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ቲኬት መቁረጥ እንደሚቻልና የጂፒሴስ ቴክኖሎጂም እንደሚገጠም የገለጹት አቶ ምትኩ ፕሮጀክቱ ባለፈው ዓመት የተጀመረ ሲሆን በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት የማዘመን ሥራው ይጠናቀቃል ተብሎ ይገመታል ብለዋል ።
የአንበሳ አውቶብስ አገልግሎት የላላና በዘመናዊ መልኩ ያልተደራጀ ቁጥጥር በመኖሩ ምክንያት አንድ አውቶቢስ በቀን 21 ዙር ደንበኞችን ማመላለስ ሲገባው 13 ዙር ብቻ የሚያመላልስ መሆኑን አቶ ምትኩ አስረድተዋል ።
ቢሮው የከተማዋን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ በአማራጭነት የሸገር አውቶቢስ፣ የአሊያንስ አውቶቢስና የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር የትራንስፖርት አገልግሎቶች እንዲጀመሩ ማድረጉን አቶ ምትኩ ገልጸዋል ።
በአዲስ አበባ ፈርቀዳጅ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ የሆነው የአንበሳ ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ለ70 ዓመት ያህል ለህብረተሰቡ አገልግሎት የሠጠ ሲሆን በአሁኑ ወቅት 500 አውቶቢሶችን በማሠማራት በ124 መሥመሮች አገልግሎት እየሠጠ ነው ።
የአዲስ አበባ ከተማ በየጊዜው እያደገች ከመምጣቷም ባሻገር የህዝብ ቁጥሯም እየጨመረ በመምጣቱ የከተማ ነዋሪው የትራንስፖርት አገልግሎት ፍላጎትም በፍጥነት እያደገ መምጣቱ የተለያዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ ።
የአዲስ አበባ ከተማ ከሰሃራ በታች ከሚገኙ 10 ትላልቅ ከተሞች አንዷ ስትሆን እ.ኤ.አ በ 2020 የከተማ ህዝብ ቁጥር አሁን ካለበት 4 ሚሊዮን 8 ሚሊዮን ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል ።
ትርጉም ሰለሞን ተስፋዬ