ምክርቤቱ ሜጋ የመስኖ ፕሮጀክቶች ፈጥነው እንዲጠናቀቁ አሳሰበ 

የህዝብ ተወካዮች ግንባታቸው የተጓተቱ ሜጋ የመስኖ ፕሮጀክቶች በአፋጣኝ እንዲጠናቀቁ አሳሰበ። 

ምክር ቤቱ ማሳሰቢያውን የሰጠው ትናንት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴርን የበጀት ዓመቱን የ10 ወራት ዕቅድ አፈጻጸም አድምጦ ነው። 

የአርጆ ዴዴሳ፣ የመቂ ዝዋይ፣ የከሰም ተንዳሆና የአድአ በቾ የመስኖ ልማትና የከርሰ ምድር ፕሮጀክቶች ግንባታቸው በመጓተቱ ተጨማሪ ወጪ እየጠየቁ መሆኑንም ገምግሟል። 

በምክር ቤቱ የተፈጥሮ ኃብት ልማትና ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ወይዘሮ ጀምበርነሽ ክንፈ እንዳሉት በ2006 ዓ.ም መጠናቀቅ የነበረባቸው ሜጋ የመስኖ ፕሮጀክቶች አልተጠናቀቁም።

"ይህም በአገሪቱ ሌሎች ፕሮጀክቶችን መገንባት የሚያስችል ተጨማሪ ወጪ እንዲወጣ እያደረገ ነው" ብለዋል።   

"ፕሮጀክቶቹ በጊዜው ተጠናቀው ቢሆን ለበርካታ ወጣቶችና ሴቶች የሥራ እድል ከመፍጠር በሻጋር አገሪቷ ከዝናብ ጥገኝነት ለመላቀቅ የምታደርገውን ጥረት በመደገፍ ትልቅ ፋይዳ ይኖራቸው ነበር" ነው ያሉት።

የግብርናውን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግና የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን ለማምረት የተያዘውን ግብ ለማሳካት የተጓተቱ ሜጋ የመስኖ ፕሮጀክቶች ፈጥነው መጠናቀቅ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።  

በድሬድዋ፣ ደምቢ ዶሎና ወላይታ ሶዶ ከተሞች እየተገነቡ ያሉ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለኀብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ባለፉት ዓመታት የመስኖ ፕሮጀክቶች የአፈጻጸም ፍጥነት አዝጋሚ እንደነበር ሲገመገም መቆየቱን አንስተዋል። 

ለፕሮጀክቶቹ መጓተት የፋይናንስ እጥረት፣ የአቅም ውስንነት፣ የልማት ተነሺዎች የካሳ ክፍያና በሚሰፍሩባቸው አካባቢዎች የመሰረተ ልማት በወቅቱ አለመሟላት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የፕሮጀክቶች ጥናትና ዲዛይን ሥራዎች የጥራት ጉድለትም ከምክንያቶቹ መካከል እንደሆኑ አመልክተዋል። 

"ችግሩን ለመፍታት በበጀት ዓመቱ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው" ያሉት ሚኒስትሩ፤ ከግንባታ በፊት የጥናት ዲዛይንና ሰነዶች ተደጋግመው እንዲፈተሹ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።

ተቋራጮችና አማካሪ ድርጅቶችም አስፈላጊውን ግብዓት በውሉ መሰረት እንዲያሟሉና በተቻለ መጠን ቀንና ሌሊት በፈረቃ እንዲሰሩ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ በውሉ መሰረት በማይሰሩ ተቋራጮችና የፕሮጀክት ኃላፊዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ ከመውሰድ ባለፈ ለልማት ተነሺዎች የሚከፈለው ካሳ ወቅቱን የጠበቀ እንዲሆን በማድረግ ረገድ የተሻለ ሥራ ተከናውኗል።

በቀጣይ የሚተገበሩ ትልልቅ የውሃ፣ የመስኖና የኤሌክትሪክ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ ኃብት በመፈለጋቸው ከነባሩ የበጀት ድልድል በበለጠ መጠን ቅድሚያ ትኩረት እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል ሚኒስትሩ።  

ምክር ቤቱ ያነሳቸውን የፕሮጀክቶች መጓተት ችግሮች ለመቅረፍ ሚኒስቴሩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም አረጋግጧል-(ኢዜአ) ።