የኢትዮ-ጅቡቲ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ከሦስት ወራት በኋላ አገልግሎት መሥጠት ይጀምራል

ከ80 በመቶ በላይ የጅቡቲ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርገው የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ከሦስት ወራት በኋላ አገልግሎት መሥጠት እንደሚጀምር  ተገለጸ ።   

ከ700 ሺ በላይ ጅቡቲያውያንን ወይንም ደግሞ 80 በመቶ የሚሆነውን ዜጋዋን ይጠቅማል የተባለው በምስራቅ አፍሪካ ብሎም በአፍሪካ በግዙፍነቱ ቀዳሚ የሆነው የኢትዮ ጅቡቲ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት፤ በቀጣይ ሶስት ወራት ውስጥ ተመርቆ ለአገልግሎት ይበቃል ተብሏል፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት እኤአ በ2015 የመሰረተ ድንጋይ የተቀመጠለት የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቱ በቻይናው ሲጂሲኦሲ የሥራ ተቋራጭ  ግንባታው እየተከናወነ ይገኛል ።  

ፕሮጀክቱ ለጅቡቲያውያን የዘመናት የውሃ ችግር መፍትሔን ይዞ የሚመጣ ነው ሲሉ የመሰረተ ድንጋዩ በተቀመጠ ሰዓት የተናገሩት የጅቡቲው ፕሬዝደንት እስማኤል ኦማር ጊሌ ተናግረዋል ።

ኢትዮጵያ ከጉርብትናም ባሻገር ለአገራቸው ህልውና የድርሻዋን እያበረከተች ያለች አገር ናት ሲሉም የጅቡቲ ፕሬዚደንት መናገራቸውን የቻይናው ሲጂቲ ኤን ዘግቧል፡፡

ከኢትዮጵያ ሃዳገላ ከተማ  እስከ ጅቡቲዋ አሊ-ሳቤህ፣ ዲክሂል፣ አርታ እና መዲናዋ ድረስ የሚዘልቀው የመጠጥ ውሃ ዝርጋታው 102 ኪሎ ሜትር የውሃ ማሠራጫ መስመር እንዳለውም ተጠቁሟል፡፡

የግንባታው በጀት ከቻይናው ኢምፖርት ኤክስፖርት ባንክ በድጋፍ የተገኘ መሆኑም ነው የተነገረው፡፡

እንዲህ አይነቱ ግዙፍ ድንበር ተሸጋሪ ፕሮጀክት በሁለት አገራት መካከል ሲገነባ ይ የመጀመሪያው ባይሆንም ከቀዳሚዎቹ ተርታ ነው ተብሏል፡፡

የምስራቅ አፍሪካን በመሠረተ ልማት በኢኮኖሚ እና እርስ በእርስ ግንኙነት ለማስተሳሰር በሚደረገው ጥረት የጎላውን ሚና እንደሚጫወት ተነግሯል፡፡

ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ በመሠረተ ልማት ትስስር በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ሲሆኑ በቅርቡ የተመረቀውን የባቡር ፕሮጀክትን ጨምሮ ሌሎች የመሰረተ ልማቶችን እያከናወኑ እንዳሉም ሲጂቲ ኤን አስነብቧል፡፡