በትግራይ የተገነባው “ሚሌ” የወርቅ ማምረቻ ፋብሪካ የሙከራ ምርት ጀመረ

በትግራይ ሰሜን ምዕራብ ዞን የሚገኘው በ700 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው "ሚሌ" የወርቅ ማምረቻ ፋብሪካ የሙከራ ምርት ማምረት መጀመሩን አስታወቀ ።

የፋብሪካው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጸጋይ አሰፋ እንዳስታወቁት፤ በትግራይ መልሶ ማቋቋም ተቋም (ትእምት) የተገነባው የወርቅ ማምረቻ ፋብሪካ ወደ ሙሉ የማምረት ሥራ ለመሸጋገር የሚያስችለውን የሙከራ ምርት ሥራ ትናንት ጀምሯል።

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ፣ ፋብሪካው በዓመት ከ40 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ያስገኛል ተብሎ ይጠበቃል። 

የፋብሪካውን የግንባታ ሥራ ለማጠናቀቅ 3 ዓመት መውሰዱን ያስታወሱት አቶ ጸጋይ፣ የክልሉን የወርቅ ሃብት ክምችት በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል የጎላ ሚና እንደሚኖረው ነው ያስረዱት ።

ፋብሪካው በቀን አራት ነጥብ አምስት ኪሎ ግራም ወርቅ የማምረት አቅም እንዳለው ጠቁመዋል፡፡

ፋብሪካው  ዙር ለ250 ሰዎች የሥራ እድል መፍጠሩም በመግለጽ ።

ኢዛና የመአድን ልማት ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኣታኽልቲ ኣርኣያ በበኩላቸው፣ “የወርቅ ማምረቻ ፋብሪካው ክልሉ የወርቅ መአድን ባለቤትነቱን ያሳያል" ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ፋብሪካው የሙከራ ምርቱን በተሳካ ሁኔታ ማከናወኑ ልዩ ስሜት እንደፈጠረባቸውና በ2010 ሙሉ በሙሉ ወደ ማምረት ሥራው እንደሚሸጋገር አመልክተዋል።

ፋብሪካው በአካባቢው የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎችን በተለያየ መንገድ ተጠቃሚ እንደሚያደርግና በተለይ የተሟላ የማህበራዊ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ በኩል ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

በፋብሪካው የሥራ እድል ካገኙ ወጣቶች መካከል ወጣት ብርሃነ ካህሳይ በፋብሪካው ውስጥ መቀጠሩ ከሚያገኘው ገቢ በተጨማሪ የሙያ ባለቤት እንደሚያደርገው ገልጸዋል።

"ከማገኘው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በተጨማሪ ከአዳዲስ ዘመናዊ የማምረቻ መሳሪያዎች ጋር እንድተዋወቅ ያደርጋል፤ ይህም የሙያ ብቃቴን ለማሳደግ ዕድል ይሰጠኛል። ” ያለው ደግሞ ሠራተኛ ወጣት ባራኪ ተስፋማርያም ነው።

የትግራይ መልሶ ማቋቋም ተቋም ግዙፍ ፋብሪካዎችን በማቋቋም ለኢኮኖሚው ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ በተጨማሪ በ10 ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል።

ፋብሪካው በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን በአስገደ ጽምብላ ወረዳ ልዩ ስሙ ‘‘ሚሌ‘‘ በተባለ ቦታ አካባቢ የተገነባ መሆኑ ታውቋል (ኢዜአ) ።