የየመን ቀውስ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ተመድ አስታወቀ

የየመን ቀውስ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የመንግስታቱ ድርጅት አስታወቀ፡፡

የተባባሩት መንግሥታት ድርጅት የመናውያንን ለመታደግ ከዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ አፋጣኝ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ሰባት ሚሊዮን የሚሆኑት ዜጎች ለረሃብ አደጋ መጋለጣቸውም ነው የተመለከተው፡፡

የቀድሞ የየመን ፕሬዘዳንት አሊ አብዱላህ ሳለህ ወደ ሳዑዲ አረቢያ መሰደድን ተከትሎ ለእርስ በርስ ጦርነት የተጋለጠችው የመን አስጊ አደጋ ላይ ደርሳለች፡፡

እኤአ ከ2015 ጀምሮ የጦር አውድማ የሆነችው የመን አስጊ ደረጃ ላይ መድረሱኗ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል፡፡

ከ10ሺ በላይ ዜጎቿን በጦርነቱ የተነጠቀችው የመን ከ20 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ዜጎቿ ለአስከፊ ችግር ተጋልጠዋል፡፡ ከዚህም ውስጥ ሰባት ሚሊዮን የሚሆኑት የረሃብ አደጋ ተደቅኖባቸዋል፡፡

ሁለት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን የመናውያን እጅግ በጣም አስከፊ ለሆነ የምግብ እጥረት እየተጋለጡ ሲሆን ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉት ህፃናት መሆናቸው የጉዳዩን አሳሳቢነት ያሳያል፡፡

ማጣሪያ ያጣው ጦርነት በኮሌራ ወረርሽን መታጀቡ ደግሞ ችግሩ ለየመናውያን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖባቸዋል፡፡

ከ300ሺ የሚበልጡ የመናውያንን ያጠቃው የኮሌራ ወረረሽን አንድ ሺ 700 የሚሆኑትን  ለህልፈት ህይወት ዳርጓል፡፡

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ድጋፍና የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ጉዳዮች አስተባባሪ ምክትል ፀሃፊ ኦ ብሬይን አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰችውን የመንን ለመታደግ ከፍተኛ ርብርብ እንደሚያፈልግ ይናገራሉ፡፡

በምግብ፣ውሃና ህክምና እጦት የመናውያን አስከፊ ህይወትን እየመሩ ነው ይላሉ፡፡ ከ55 በመቶ በላይ የሚሆነው የአገሪቱ የህክምና መሠረተ ልማቶች በጦርነቱ ምክንያት በመውደማቸውና በመፈራረሳቸው እንዲሁም በገንዘብ እጦት ከአገልግሎት ውጭ መሆናቸውን ኦ ብሬይን ገልፀዋል፡፡

በመሆኑም በአገሪቱ ውስጥ ካሉት ሆስፒታሎች ከግማሽ በታች ያህሉ ብቻ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ እነዚህም ቢሆኑ ታዲያ የባለሙያ፣ የመድኃኒትና የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት ስለሚያጋጥማቸው ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት መቸገራቸው ነው የሚነገረው፡፡

ከ30ሺ በላይ የጤና ሠራተኞችም በገንዘብ እጦት የዓመት ደመወዛቸው አልተከፈላቸውም፡፡ እናም ባሉትም ጥቂት የህክምና አገልግሎት መስጫ ተቋማት አገልግሎቱን ለመስጠት አስቸጋሪ ሆኗል፡፡

16 ሚሊዮን የመናውያን በቂ የመጠጥ ውሃ ስለማያገኙና ንፅህናቸውን ለመጠበቅ በመቸገራቸው በአገሪቷ እየተዛመተ ላለው የኮሌራ ወረርሽን የመጋለጥ ዕድላቸው ሰፊ ነው፡፡ 

ይህን የየመናውያንን ስቃይ ለማቆም የተባበሩት መንግስታ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የመፍትሔ እርምጃ ሊወስድ ይገባል ብለዋል ኦ ብሬይን፡፡ ጦርነቱን ለማስቆም የሚስችል ጠንካራ እርምጃ በአፋጣኝ እንዲወሰድ አሳስበዋል፡፡

አገሪቱን ከገባችበት ቀውስ ለማውጣት የተቀናጀና ዘላቂ የሆነ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ የምክትል ፀኃፊው ልዩ መልዕክተኛ እስማኤል ዑድ ሼክ አህመድ ተናግረዋል፡፡

በየመን ጦርነት ውስጥ በቀጥታና በተዘዋዋሪ እየተሳተፉ የሚገኙ አካላት የሰብዓዊ መብት ህግጋትን በማክበር ለሰብዓዊ ድጋፍ የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰቡም ለየመን ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም የየመናውያንን ህይወት ለመታደግ ድጋፉን እንዲያደርግ ጥሪ ቀርቧል፡፡