በደቡብ ክልል ከ497 ሺህ በላይ ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሰማሩ

በደቡብ ክልል ከ497 ሺህ በላይ ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሰማርተዋል

በደቡብ ክልል በሶስት ዞኖች ብቻ ከ497 ሺህ በላይ ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት መሰማራታቸዉን የክልሉ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ገለጸ ::

በሃዲያ ዞን ከ2 መቶ ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች 100 ሺህ ችግኞችን መትከላቸዉ ጽሕፈት ቤቱ አስታውቋል ፡፡

ወጣቶች በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ላይ ከ174 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎች ላይ መሳተፋቸውም ነው ያመለከተው ፡፡

በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በ20 የስራ ዘርፎች ላይ አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን፤ እስከአሁን ድረስ የተሰሩት የጉልበት ስራዎች በገንዘብ ሲሰላ ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት እንዳለውም አስታውቋል ፡፡

ወጣቶች ቀሪ የእረፍት ጊዜቸውን በሌሎች ተግባራት ላይ በንቃት በመሳተፍ ለሌሎችም ወጣቶች አርአያ የሚሆን ተግባር እያከናውኑ እንደሆነም ነው ያስረዳው ፡፡

በጉራጌ ዞን በዞኑ ባሉት 444 ቀበሌዎች ከ218 ሺ በላይ ወጣቶች እንዲሳተፉ ከታቀደው ውስጥ ከሐምሌ 1/ 2009 ዓመተ ምህረት አንስቶ ከ185 ሺ በላይ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በ20 የአገልግሎት ዘርፎች እንደተሰማሩ ተመልክቷል ፡፡

በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ የዩኒቨርሲቲ ፣የኮሌጅና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች፣የመንግስት ሰራኞች እንዲሁም የወጣት አደረጃጀቶች ተሳታፊ መሆናቸውን ነው የተገለጸው ፡፡

ወጣቶቹ የተሳተፉባቸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችም ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚገመት ተመልክቷል፡፡

በደቡብ ኦሞ ዞን ደግሞ በተያዘው የክረምት ወቅት ከ112 ሺህ በላይ ወጣቶች በበጎ ፈቃድ ስራ ላይ መሳተፋቸውን ገልጿል ፡፡

ወጣቶች በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራ ላይ መሳተፍ በመቻላቸው በአካባቢያቸው በሚከናወኑ የልማት ስራዎች ላይ የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማቸው ያደርጋል ነው የተባለው ፡፡

በዞኑ 112 ሺህ 642 ወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራ ላይ የተሰማሩ ሲሆን፤ከነዚህም 33ነጥብ 8 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸዉ ነው የገለጸው ፡፡

በዞኑ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከሚሰማሩ ወጣቶች ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ስራ ለማከናወን ታቅዶ እስካሁን ባለው አፈፃጸም 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር የሚገመት ስራ ተከናውኗል ብለዋል ፡፡

በወጣቶች ከሚከናወኑ የልማት ስራዎች ውስጥ የክረምት የማጠናከሪያ ትምህርት፣ የአካባቢ ጥበቃ፣ መንገድ ደህንነት፣ ስፖርት ልማት፣ መልካም አስዳደር እና ሌሎችም ተዛማጅ ስራዎች ተጠቃሽ ናቸው ፡፡