የሰሜን ኮሪያ ሁለተኛው የሚሳኤል ሙከራ ሁሉንም የአሜሪካ ግዛቶች ስጋት ውስጥ የሚከት ነው

ሰሜን  ኮሪያ  ለሁለተኛ ጊዜ ያደረገችው  ስኬታማ  የአህጉር ኣቋራጭ  የሚሳኤል ሙከራ    ሁሉንም  የአሜሪካ  ግዛቶች  ኢላማ  ማድረግ የሚችልና  ስጋት ውስጥ  ሊከት የሚችል ብርቱ  ማስጠንቀቂያ   መሆኑ  ተመለከተ  ።

የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ ኡን እንደተናገሩት  ሰሜን ኮሪያ  ለሁለተኛ ጊዜ  የሞከረችው አህጉር አቋራጭ   ሚሳኤል ሁሉንም  የአሜሪካን  ግዛቶች  ኢላማ  ማድረግና ጥቃት መሰንዘር  የሚያስችል  ነው   ።    

ሰሜን  ኮሪያ  ለሁለተኛ  ጊዜ  ያደረገችው የቦለስቲክ  የሚሳኤል ሙከራ  የመጀመሪያውን ካደረገች  ከሦስት   ሳምንታት ቆይታ በኋላ   የተከናወነ መሆኑ  ተገልጿል  ።    

የአሜሪካው  ፕሬዚደንት  ዶናልድ  ትራምፕ  የሰሜን ኮሪያን  የሚሳኤል  ሙከራ አደገኛና  ኃላፊነት  የጎደለው የሰሜን ኮርያ መንግሥት  ድርጊት መሆኑን ገልጸዋል  ።   

ቻይና በበኩሏ  የሚሳኤል  ሙከራውን  በማውገዝ   ሁሉም አካላት  ከተመሳሳይ  ድርጊት  በመቆጠብ   ውጥረትን  እንዲያስወግዱ   ጥሪ አቅርባለች  ።

ሰሜን ኮርያ   የአሁኑ የአገር አቋራጭ  ሚሳኤሏ   ለ 47  ደቂቃዎች ያህል  ከመሬት  በ 3ሺህ 724  ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ  የተወነጨፈ  መሆኑ ተረጋግጧል  ።   

 

የሰሜን  ኮርያ  ማዕከላዊ  የዜና ወኪል ባቀረበው ዘገባ  ላይ  የሰሜን ኮርያ ፕሬዚደንት በቴሌቭዚን ቀርበው   የአህጉር አቋራጭ  ሚሳኤሉ  የትኛውንም የአሜሪካ   ግዛት ለማጥቃት እንደሚያስችል  በኩራት   ተናግረዋል  ።

ሚሳኤሉ  ሃውሶንግ  -14   የሚል  ስያሜ ያላው ሲሆን   ከሦስት ሳምንታት በፊት  ከተተኮሰው ሚሳኤል ጋር ተመሳሳይነት  አለው ።

ሰሜን  ኮርያ  አሁን  የተኮሰችውን  አህጉር አቋራጭ  ሚሳኤል አቅም በተመለከተ  የሚወጡ  መረጃዎች እንደሚያሳዩት  ሚሳኤሉ  10ሺህ 400  ኪሎሜትሮችን  የሚጓዝ  መሆኑንና   ከሰሜን ኮሪያ ሰሜናዊ ምስራቅ  ከሆነችው  ራንሶን  ሲተኮስ  የኒዎርክ ከተማን   ኢላማ ውስጥ ማስገባት  እንደሚችል  ተገልጿል ።

አሜሪካ ያወጣችው   ሪፖርት  እንደሚያመለክተው  ሰሜን ኮርያ የተኮሰችው ሚሳኤል ሙፒዮንግ ኒ ከተባለችውን   የሰሜን ኮርያ ሥፍራ ሲሆን የተለያዩ  ዓለም አቀፍ  የመገናኛ ብዙሃን ካወጡትና የሚሳኤል ተኩሱ የተካሄደው  ኩሶንግ  አካባቢ  ነው ከሚለው ዘገባዎች  የተለየ መሆኑ ተመልክቷል ።

እንደ አሜሪካ  ገለጻ   ሰሜን ኮርያ  አሁን ያደረገችው  የሚሳኤል ሙከራ  ባልተለመደ  ሰዓት ሲሆን  አገሪቷ  የሚሳኤል ሙከራዋን  በሌሊት በማካሄድና  ሌላ አደናጋሪ  ሚሳኤሎችን  በተለያዩ   አካባቢዎች በማስቀመጥ ታዛቢዎች  ትክክለኛ መረጃ እንዳያገኙ  የሚያስችል ሥራ ሠርታለች ።

በሰሜን ኮርያ የተተኮሰው ሚሳኤል በሰማይ ላይ 10 ሺህኪሎሜትሮችን በማቋረጥ   በመጨረሻ  መዳረሻውን  በጃፓን ባህር ላይ አድርጓል ።