ሰሜን ኮርያ ከአሜሪካ ለሚሰነዘርባት ማስፈራሪያ ምላሽ ለመሥጠት እየተዘጋጀች ነው

ሰሜን ኮርያ  ከአሜሪካ  ለሚሰነዘርባት ማስፈራሪያ ምላሽ ለመሥጠት አስፈላጊውን  ዝግጅት  እያደረገች  እንደምትገኝ  አስታወቀች ።

ከአሜሪካ ለሚሰነዘርባት ዛቻና ማስፈራሪያ ምላሽ ለመስጠት እየተጋች ነው በማለት ፒዮንግያንግ ወታደራዊ አቅሟን ማጎልበቷን ትገልጻለች ፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ማዕቀቦች በመጣስ በተደጋጋሚ የሚሳኤል ሙከራዎች በማድረግ የምትወቀሰው ሰሜን ኮርያ የአሜሪካ ከተሞችን ለመምታት የሚችሉ አህጉር ተሻጋሪ ሚሳኤሎችን በመሞከር አሜሪካን አስጠንቅቃለች፡፡

በቅርቡም በፓስፊክ ደሴት በሚገኘው ጉኣም የአሜሪካ ወታደራዊ ቀጣና የሚሳኤል ጥቃት ለማድረስ መዛቷ ይታወሳል፡፡

አሜሪካ በበኩሏ በቀጣናው ሠላም ለማስፈን ከሰሜን ኮርያ ጋር አንዴ በጠረጴዛ ዙርያ በድርድር በሌላ ጊዜ ደግሞ ወታደራዊ አቅምን እንደአማራጭ እንደምትጠቀም ስትናገር ተደምጧል፡፡

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ፒዮንግያንግ ለውይይት ዝግጁ አይደለችም በማለት ወታደራዊ ኃይልን አማራጭ ሲያደርጉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን አገራቸው ለውይይት ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል፡፡

አሁንም ችግሩ በውይይት ቢፈታ የተሻለ አማራጭ እንደሆነ አሜሪካ ማስገንዘቧን ነው የተደመጠው፡፡

ዋሽንግተን ከፒዮንግያንግ ጋር ለመወያየት እንደምትፈልግ በከፍተኛ ባለሥልጣኖቿ አማካኝነት ታስረዳለች፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰንና የመከላከያ ሚኒስትሩ ጀምስ ማቲስ አሜሪካ በሰሜን ኮርያ ላይ ሰላማዊ የግፊት ዘመቻ እያደረገች እንደሆነ መናገራቸውን ሲ ኤን ኤን ዘግቧል፡፡

አሜሪካ የሰሜን ኮርያ መንግስትን የመቀየር ፍላጎት እንደሌላት ሚኒስትሮቹ ጠቁመው የኒውክሌር ልማቱ እንዲቀዛቀዝና እንዲቆም ግን ፅኑ ፍላጎት አላት ብለዋል፡፡

ዋሽንግተን በርካታ ዓመታትን በስቃይ እያሳለፈ የሚገኘውን የሰሜን ኮርያ ህዝብ የመጉዳት ዓላማ እንደሌላትም ነው የተመለከተው፡፡  

ዋሽንግተን እንዲህ ብትልም ታዲያ ፒዮንግያግ አራት ሚሳኤሎችን ወደ ጉኣም ለማስወንጨፍ የመጨረሻውን ዝግጅት ማድረጓን አስታውቃለች፡፡ 

የዝግጅቱ ሂደትና ዕቅድ ለአገሪቱ መሪ ኪም ዮንግ ኡን መቅረቡም በዘገባው ተጠቅሷል፡፡ ሚሳኤል የማስወንጨፉ እርምጃ መች እንደሚተገበር ቀኑ ባይገለፅም፡፡

ሚኒስትሮቹ ፒዮንግያንግ ለውይይት በሯን ክፍት እንድታደርግ ቻይና የሚጠበቅባትን እንድትወጣ አሳስበዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ዙርያ ዓለም ከቻይና ብዙ ይጠብቃል ማለታቸውም ነው የተሰማው፡፡

ቻይና በሁለቱ አጋራት ንትርክ ውስጥ ከመግባት መታቀብን መምረጧን ዘገባው አስነብቧል፡፡

የአሜሪካ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለስልጣንና የአሜሪካና የደቡብ ኮርያ ጥምር ኃይል ሰብሳቢ ጄኔራል ጆሴፍ ዳንፎርድ ደቡብ ኮርያ ገብተዋል፡፡

የጄኔራል ዳንፎርድ የሴዑል ጉብኝት የሁለቱ አገራት ጦር በጋራ በሚንቀሳቀሱባቸው ጉዳዮች ዙርያ መምከርን ዋና ዓላማው ያደርጋል ተብሏል፡፡