የአዲስ አበባ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች መክፈያ ቀን ዛሬ ይጠናቀቃል

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደረጃ "ሐ" ግብር ከፋዮች ከ98 ከመቶ በላይ የሚሆኑት የሚጠበቅባቸውን ግብር መክፈላቸውን የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ አስታወቀ።

በአዲስ አበባ የደረጃ "ሐ" የግብር ከፋዮች በቀን ገቢ ግምት ቅሬታ በተፈጠረ የስራ ጫናና በግብር ከፋዮች ይራዘምልን ጥያቄ ለተጨማሪ 10 ቀናት ተራዝሞ የነበረው የግብር መክፈያ ቀን ዛሬ ይጠናቀቃል።

በከተማዋ ካሉት ከ59 ሺህ በላይ የደረጃ "ሐ" ግብር ከፋዮች ውስጥ ከ58 ሺህ በላይ የሚሆኑት የከፈሉ ሲሆን ይህም በመቶኛ ሲታይ 98 በመቶ ነው።

በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽህፈት የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ፋሲካ በላይ  እንደገለጹት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ በሀምሌ ወር 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ ከ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ተናግረዋል።

በተጨማሪም በተራዘመው 10 ቀናት ውስጥ  ከ17 በመቶ በላይ የደረጃ "ሐ" ግብር ከፋዮዎች መክፈላቸው ጠቁመዋል።

እንደ አቶ ፋሲካ ገለጻ  በተቀመጠላቸው ጊዜ መሰረት የሚጠበቅባቸውን ግብር ያልከፈሉ  የደረጃ "ሐ" ግብር ከፋዮች ከነገ ነሐሴ 11/2009 ዓ.ም ጀምሮ ከቅጣት ጋር ይከፍላሉ።

የደረጃ "ለ" ግብር ከፋዮች የግብር መክፈያ ጊዜ ነሐሴ 1 እስከ ጳጉሜ 5 ቀን 2009 ዓ.ም ድረስ መሆኑን አውቀው በመጨረሻው ቀን የሚደርሰውን መጨናነቅ ለማስቀረት ከወዲሁ እንዲከፍሉም አሳስበዋል።(ኢዜአ)