የቻይና ኩባንያ በአንጎላ ትልቁን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ለመገንባት ተስማማ

የቻይና የኮንስትራክሽን  ኩባንያ በአንጎላ የሀገሪቱ ትልቁን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ  ለመገንባት  ከስምምነት ላይ ደርሷል፡፡

የኃይል ማመንጫው 2 ሺ 172 ሚሊየን ኪሎዋት የኃይል አቅርቦትን ይሰጣል ተብሏል፡፡

የአፍሪካ  ሀገራት ግንባር ቀደም የልማት እና የንግድ አጋር የሆነችው ቻይና በአንጎላ አዲስ የሃይደሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ በመገንባት የሀገሪቱ ቀዳሚ የንግድ እና የልማት አጋር መሆኗን አረጋግጣለች፡፡

 በአንጎላ ትልቁን የሀይደሮ ኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ለመገንባት ከቻይና የኮንሰትራክሽን ኩባንያ ጋር ከስምምነት ላይ መድረሷን ይፋ ባደረገችበት ወቅት የአንጎላው ፕሬዝዳንት ጆሴ ኤዱዋርዶ ዶስ ሳንቶስ በቦታዉ ተገኝተዉ  እንዳሉት  በካኩሎ ካባሳን የሚገነባው የሀገሪቱ ትልቁ የሀይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግንባታ ሲጠናቀቅ በአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ ወሳኝ ሚናን እንደሚጫወት ገልጿል፡፡

በሰሜናዊ አንጎላ ክዋንዛ ውስጥ የሚገነባው የካኩሎ ካባሳ  የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ጣቢያ የአንጎላን ከፍተኛ የሆነ የኃይል እጥረት ቀስ በቀስ እንደሚቀንስ የታመነበት ሲሆን  በአጠቃላይ  ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫው ግንባታ አንጎላ  4 ቢሊዮን  የአሜሪካን ዶላር ወጪ ታደርጋለች፡፡

የግድቡ ግንባታ በተጠናቀቀ ማግስትም አንጎላ 2 ሺ172 ሚሊዮን ኪሎዋት የኃይል አቅርቦትን ታገኛለች፣ ይህም የአንጎላን የኃይል አቅርቦት ችግር ከመቅረፉም ባለፈ በአፍሪካ ጥሩ የኃይል አቅርቦት ካላቸው ሀገራት መካካል አንዷ ያደርጋታል፡፡

የኤሌክትሪክ ማመንጫ ጣቢያው ጌዙውባ  በተባለ የቻይና የግንባታ ድርጅት የሚከናወን ነው፡፡

የኃይል ማማንጫዉ ስራ አስኪያጅ አጉስቶ ሳልቫዶር እንዳሉት ደግሞ የካኩሎ ካባሳ  ተጓዳኝ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ግንባታ የኤሌክትሪክ  ኃይል እጥረት ችግርን  በሚገባ ከመቅረፉም ባለፈ  በሀገሪቱ እና  በአከባቢው ላሉ ዜጎች የሥራ ስምሪት  እድልን ያሰፋል፣ በተጨማሪም ለአካባቢው ሠራተኞች የሙያ  ክህሎት ሥልጠናን ይሰጣል ሲል ተደምጠዋል፡፡

የኃይል ፕሮጀክቱ ተጠናቅቆ  ለአገልግሎት ዝግጁ ሲሆን  ቢያንስ 10,000 ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚሰጥ  ይጠበቃል፣ የፕሮጀክቱ ግንባታም  በሰባት ዓመታት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ይገመታል፡፡

የኃይል ፕሮጀክቱ  የቻይና  መንግስት በአንጐላ እያከናውናቸው  ከሚገኙ በርካታ ኢንቨስትመቶች መካካል አንዱ ሲሆን ቻይና በአንጎላ እስካሁን  ድረስ ለተለያዩ መሰረተ ልማቶች እና  ተጓዳኝ ስራዎች 50 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ወጪ ማድረጓን ሲ ጂ ቲ ኤን ዘግቧል፡፡