የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጨማሪ የበረራ መዳረሻዎችን በቻይና ከተሞች ሊከፍት ነው

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቅርቡ ተጨማሪ የበረራ መዳረሻዎችን በቻይና ከተሞች ሊከፍት ነው።

ቻይና ተግባራዊ  ባደረገችው የቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ ከአፍሪካ አገራት ጋር ያላትን የህዝብ ለህዝብ ትስስር ለማጠናከር መወሰኗን ተከትሎ ነው አየር መንገዱ መዳረሻውን የሚያሳድገው።

እናም አየር መንገዱ በደቡብ ቻይና ሼንጄን፣ በምዕራብ ቾንቺን እንዲሁም በማዕከላዊ የአገሪቱ ክፍል ጄንጁ ከተሞች መዳረሻውን ለማድረግ የአዋጪነት ጥናት አጠናቋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቻይና፣ ሰሜን ኮሪያና ሞንጎሊያ ቀጣና ዳይሬክተር አቶ ያሬድ በርታ እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት አየር መንገዱ በአገሪቱ አምስት መዳረሻዎች ሲኖሩት በቅርቡም ሼንጄንን ስድስተኛ መዳረሻው ያደርጋል።

ይህ ደግሞ በአፍሪካ 56 የመዳረሻ ከተሞች ያሉት አየር መንገዱ እነዚህን ከተሞች በዓለም ሁለተኛዋ ግዙፍ የኢኮኖሚ ባለቤትና የአህጉሪቱ ቀዳሚ የንግድና ኢንቨስትመንት አጋር ከሆነችው ቻይና ጋር ይበልጥ የሚያስተሳስር ይሆናል ።