ግብጽና ሱዳን የድንበር ማስጠበቅ ስራን ለማጠናከር ተስማሙ

ግብጽና  ሱዳን ድንበር ማስጠበቅ ሥራን ለማጠናከር የሚያስችል  ስምምነት አደረጉ

ግብጽና ሱዳን የድንበር ማስጠበቅ ስምምነት እንዲኖራቸው የጥምር ጦር ኮሚቴ  አቋቁመዋል ተብሏል፡፡

የግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታ አልሲሲ እና የሱዳኑ መከላከያ ሚኒስትር ዋድ ኢብን አውፍ በካይሮ ተገናኝተው ከተወያዩ በኋላ ሀገራቱ የድንበር ጥበቃ ስራን በጋራ ለመስራት ከስምምነት ደርሰዋል፡፡

ሁለቱ ሃገራት ከድንበር ጥበቃው ባሻገር የጋራ ጥምር ጦር ኮሚቴ ለማቋቋም የሚያስችል ስምምነት እንዳደረጉም የግብጽ ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ቃል አቀባይ ገልጸዋል፡፡

በስምምነቱ ላይ ከአል ሲሲ እና ኢብን አውፍ በተጨማሪ የግብጽ መከላከያ ሚኒስትር ሜጀር ጄነራል ሳዲቅ ሱብሂ እና በካይሮ የሱዳን አምባሳደር አብደል ሞሃመድ አብደል ሃሊም ተገኝተዋል፡፡   

እንደ ቃል አቀባዩ አላ ዩሱፍ ገለጻ ሱዳን ከግብጽ ጋር የጀመረችውን የሁለትዮሽ ተግባራት አጠናክራ የመቀጠል ከፍተኛ ፍላጎት አላት፡፡     

በውይይቱ ወቅት የሱዳኑ መከላከያ ሚኒስትር ኢብን አውፍ ግብጽ በአረቡ አለም አንድነት ላይ ያላትን ቁልፍ ሚና ሱዳን ታደንቃለች ማለታቸውንም ቃል አቀባዩ አያይዘው ገልጸዋል፡፡

ግብጽ ለመላው ለሱዳን ብቻ ሳይሆን ለመላው አረብ ሃገራት ደህንነት ዋነኛ ተዋናይ ነችም ብለዋል ኢብን አውፍ፡፡ 

በሁለቱ ሃገራት ግንኙነት ላይ እንቅፋት ሊሆን የሚችልን ማንኛውም ሃይል ለመመከት የሚያስችል ጥምር ጦር ለመመስረት ከስምምነት ላይ ደርሰዋልም ነው የተባለው፡፡

ከውይይቱ በኋላ አልሲሲ ሁለቱ ሃገራት ለደረሱበት ልዩና ታሪካዊ ስምምነት የሱዳኑ አቻቸው ፕሬዚዳንት ኦመር አልበሽር ከፍተኛውን ሚና ተጫውተዋልና ሊመሰገኑ ይገባልም ብለዋል፡፡

የግብጽ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከጎረቤት ሃገራት ጋር መልካም ግንኙነት መመስረትን የሚያበረታታ ሲሆን በጎረቤት ሃገራት የውስጥ ጉይ ጣልቃ መግባትን ፈጽሞ ይከለክላል ያሉት ቃል አቀባዩ ከሱዳን ጋር የተደረገው ስምምነትም በዚህ መልኩ መከናወኑንም ጠቁመዋል፡፡

ሃገራቱ ሌሎች ተጨማሪ ስምምነቶችን እንደሚያደርጉም ቃል አቀባዩ ኣላ ዩሱፍ ገልጸዋል ( ምንጭ: ሱዳን ትሪቡን) ፡፡