በአዲሱ በጀት ዓመት 15 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ መድሓኒቶችና የህክምና መገልገያ መሣሪያዎችን ግዥ ለማከናወን አቅዶ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ የመድሓኒት ፈንድና አቅርቦት አጄንሲ አስታወቀ ።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሎኮ አብርሃም ለዋልታ እንደገለጹት፤ 15 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ 1ሺ 400 አይነት መድሓኒቶችንና የህክምና መገልገያ መሣሪያዎችን ግዥ በማከናወን ለተጠቃሚዎች ለማሠራጨት ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል ።
ባለፈው የበጀት ዓመት ኤጀንሲው 13 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ መድሓኒቶችንና የህክምና መሣሪያዎችን ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲውሉ ማድረጉን የጠቆሙት ዶክተር ሎኮ መድሓኒቶቹ ከአገር ውስጥና ከውጭ የተገዙ ናቸው ብለዋል ።
ኤጄንሲው በአገሪቱ እጅግ ተፈላጊ የሆኑ 420 የሚሆኑ የተለያዩ የህክምና መገልገያ መሣሪያዎችን በመለየት የህክምና ተቋማት በቀጥታ ያለንም ውጣ ውረድ የሚገዙበትን የአሠራር ሁኔታን መዘርጋቱን ዶክተር ሎኮ አስረድተዋል ።
በተለይ ትልልቅ ካፒታል የሚጠይቁትን የህክምና የመገልገያ መሣሪያዎችን በዓመት ሦስት ጊዜ በጨረታ እንዲገዙ በማድረግ በመላ አገሪቱ የሚገኙ ተቋማት በአግባቡ እንዲስተናገዱ ጥረቶች እየተካሄዱ መሆኑን ዶክተር ሎኮ ገልጸዋል ።
እንደ ዶክተር ሎኮ ገለጻ ኤጀንሲው ዓምና የነበረው 63 በመቶ የመድሓኒት አቅርቦትን በ2010 95 በመቶ ለማድረስም ዕቅድ ወጥቶ ተግባራዊ ለማድረግ ከወዲሁ እንቅስቃሴዎች ጀምረዋል ።
እስካሁን ድረስ በአገር ውስጥ የሚገኙት የመድሓኒት አምራቾች 10 በመቶ ብቻ የሚሆነውን የመድሓኒት አቅርቦት ብቻ እየሸፈኑ እንደሚገኙ ጠቁመው፤በአገሪቱ የመድሓኒት አምራቾች እንዲበራከቱ በርካታ የማበረታቻ ሥርዓትን መዘርጋቱን አብራርተዋል ።
የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ከ 80 በመቶ በላይ የሆኑ መድሓኒቶች የጥራት ደረጃቸው ተረጋግጦ ወደ አገር ውስጥ እንደሚገቡ አመልክተዋል፡፡
የመድሓኒቶችን የጥራት ደረጃ ይበልጥ ለማረጋጋጥ ኤጄንሲው ከሌሎች አገር አካላት በተጨማሪ የራሱን የጥራት ማረጋገጫ ላብራቶሪ በማደራጀት ላይ መሆኑን አስታውቀዋል ።
የመድሓኒት ፈንድና አቅርቦት አጄንሲ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸውን መድሓኒቶችና የህክምና መገልገያ መሣሪያዎችን የሚያስወግድበት ሥፍራ የሌለው በመሆኑ ለረጅም ጊዜ ሲቸገር የቆየ ሲሆን በመጪው ዓመታት 8 የማስወገጃ ማዕከላትን ለማስገንባት ዕቅድ ማውጣታቸውን ጠቁመዋል ።