ታንዛኒያ የትምህርት ጥራት ጉድለት ባሳዩ 130 ትምህርት ቤቶች መዝጋቷን አስታወቀች

ታንዛኒያ የሃገሪቱን የትምህርት ጥራት ደረጃ አላሟሉም ያለቻቸውን ከአንድ መቶ ሰላሳ በላይ ትምህርት ቤቶች መዝጋቷ ተነገረ፡፡

የሃገሪቱን ስርዓተ ትምህርት በአግባቡ አልተገበሩም የተባሉ አንድ መቶ ሰላሳ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ መደረጉን ነው የዳሬሰላም ትምህርት ጽህፈት ቤት ኦፊሰር ሃሚስ ሊሱ ተናግረዋል፡፡

እንደ ሚስተር ሊሱ ገለጻ ከሆነ እርምጃው በትምህርት ተቋማቱ ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶች እንዲስተካከሉና የትምህርት ጥራት ደረጃው እንዲጠበቅ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡

እርምጃው ከተወሰደባቸው የትምህርት ተቋማት መካከል አብዛኞቹ የትምህርት ጥራት ችግር እንዳለባቸውም ሚስተር ሊሱ ጠቁመዋል፡፡

የእነዚህ ትምህርት ተቋማት ባለቤቶች ለትምህርት ደረጃው የሚመጥኑ የመማሪያ ክፍሎችን መገንባት ሲገባቸው በጠባብ የእንግዳ ማረፊያዎች ውስጥ ሲያስተምሩ ቆይተዋል ተብሏል፡፡

የትምህርት ተቋማቱ ከተማሪዎች ምዝገባ ጊዜ አንስቶ የሃገሪቱን የትምህርት ጥራት ደረጃ የማይመጥኑ አሰራሮችን የሚከተሉ ስለመሆናቸው በክትትል ተደርሶባቸዋል፡፡

ተማሪዎቹ የሚማሩባቸው ክፍሎችና አጠቃላይ የትምህርት ቤቶቹ አካላዊ ቁመና ለተማሪዎቹ ደህንነት ስጋት ሊሆኑ የሚችሉ አይነት መሆናቸውም ተመልክቷል፡፡

አብዛኞቹ የትምህርት ተቋማት የመማሪያ ክፍሎች፣ የመጫወቻ ሜዳ፣ መፀዳጃ ቤቶችና መሰል የትምህርት መሠረተ ልማት ያልተሟላላቸው እንደሆኑም ተገልጿል፡፡        

በትምህርት ቤቶቹ ላይ የሚስተዋለው ችግር በዚህም ሳያበቃ ወላጆችን ለተጨማሪ ወጪ የሚዳርጉ አንዳንድ የማጭበርበር ተግባራንም መከናወናቸው መታወቁ ተወስቷል፡፡

በዚህም ወላጆችና ተማሪዎች በከፍተኛ ሁኔታ መማረራችውን ሚስተር ሲሙ አያይዘው ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ትምህርት ቤቶቹ በብሄራዊ ፈተናዎች ወቅት የተማሪ ውጤትን የሚያዛቡ ተግባራትን በተለያዩ ዘዴዎች ሲያከናውኑ ተደርሶባቸዋል፡፡

እነዚህና መሰል ችግሮች ላለፉት አስር አመታት የታንዛኒያን የትምህርት ጥራት  ሲፈታተኑ የቆዩ መሆናቸውንም ሚስተር ሊሙ አስረድተዋል፡፡

በመሆኑም የትምህርት ተቋማቱ ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ መውሰዱ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ለአሁን አንድ መቶ ሰላሳ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ የተደረጉ ሲሆን እርምጃው በሌሎችም ላይ የሚቀጥል ይሆናል ነው የተባለው፡፡ 

እርምጃ በተወሰደባቸው የትምህርት ተቋማት ሲማሩ የነበሩ ተማሪዎች የማስተማር ፈቃድ ወደ ተሰጣቸው ተቋማት እንዲዛወሩ እየተደረገ መሆኑንም ሚስተር ሲሙ ጠቁመዋል፡፡( ምንጭ: ዘ ሲቲዚን )