ያለደረሰኝ ግብይት የፈፀሙ 90 ድርጅቶች ተያዙ

ያለደረሰኝ ግብይት የፈፀሙ 90 ድርጅቶች መያዛቸውን የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

የባለስልጣኑ የትምህርትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኤፍሬም መኮንን ከዋልታ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት ባለስልጣኑ ከደረሰኝ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ ባካሄደው ሕግ የማስከበር ሥራ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የደረጃ ቁጥራቸው 90 የሆኑ “ሀ” እና “ለ” ግብር ከፋይ ድርጅቶች ያለደረሰኝ ግብይት ፈጽመዋል፡፡

ከሐምሌ 1፣ 2009 ዓ.ም. እስከ መስከረም 30፣ 2010 ዓ.ም. ድረስ ባሉት ሶስት ወራት በፌዴራልና ክልሎች በድርጊቱ የተሳተፉ 131 ተጠርጣሪዎችም በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አቶ ኤፍሬም አክለው ገልጸዋል፡፡

በድርጊቱ ላይ የተሳተፉ ግለሰቦችም እያንዳንዳቸው 50 ሺህ ብር እንዲከፍሉ እንደተደረገና በጥፋታቸው ደግሞ ጉዳያቸው  ለፌዴራል አቃቤ ሕግ ለወንጀል ምርመራ መላኩን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ያለደረሰኝ ግብይት መፈፀም በእንዳንዱ ደረሰኝ ከ25-50ሺህ ብር እንዲሁም ከ3-5 ዓመት ጽኑ እስራት እንደሚያስቀጣ በሕግ ተደንግጓል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ በሩብ ዓመቱ ሐሰተኛ ደረሰኝ በመጠቀም ከመንግስት ካዝና ተመላሽ የጠየቁ 81 ተጠርጣሪ ድርጅቶች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ ጥፋተኛ ድርጅቶቹ አስከ 100 ሺህ ብርና ከ7-10 ዓመት ጽኑ አስራት እንደሚቀጡና በቀጣይም ጉዳያቸው በምርመራ ኦዲተሮችና የታክስ ኦዲተሮች ታይቶ ከ100ሺህ ብር በላይ ተመላሽ የጠየቁ ድርጅቶች የጠየቁትን ገንዘብ መጠንና ከ10 አስከ 15 ዓመት እስራት እንደሚጠብቃቸው አቶ ኤፍሬም ገልጸዋል፡፡

ባለስልጣኑ በተያዘው ሩብ ዓመት ሕግ የማስከበር፣ የማስተማርና ግንዛቤ የመፍጠር ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥልና የግብር ከፋዩ ማህበረሰብ በሕግ አግባብ ኃላፊነቱን እዲወጣ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡