የዚምባብዌ ወታደራዊ ኃይል የአገሪቱን ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ በቁጥጥር ሥር አዋለ

የዚምባብዌ ወታደራዊ ሃይል የብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያውን በቁጥጥሩ ሥር አውሎታል፡፡ የመንግስት ተቋማት የሚገኙባቸውን መንገዶችም ዘጋግተዋል፡፡

ወታደራዊ ኃይሉ ድርጊቱን መፈንቅለ መንግስት አለመሆኑን ሲገልጽ ፕሬዚደንቱም ደህንነታቸው እንደተጠበቀ ነው ተብሏል፡፡

ሰውየው 94ኛ ዓመት የልደት በዓላቸውን ለማክበር የቀሩ ሦስት ወራትን በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ፡፡

ከሰሞኑ ምክትላቸውን ኤመርሰን ማንጋዋን ከስልጣን ማንሳታቸውና በምትኩ ባለቤታቸውን ግሬስ ሙጋቤን መተካታቸው በአገሪቱ የቅርብ ሰዎቻቸውንም ሆነ ተቃዋሚዎቻቸውን በአንድ ጎራ መድቦ ሲያነጋግር የሰነበተ ጉዳይ ሆኗል፡፡

ፕሬዚደንቱ ለደህንነታቸው በመስጋት ይህን ውሳኔ በፓርቲያቸው በኩል እንዳስተላለፉ ተነግሯል፡፡ ነገር ግን በፖለቲካ ተንታኞች ዘንድ ሙጋቤ ሥርወ መንግስታቸውን ለማስቀጠል የተጠቀሙት ነው ተብሏል፡፡

የፕሬዚደንት ሙጋቤ የሥልጣን ላይ ቆይታ በተራዘመ ቁጥር ተቃውሟቸውን ሲያንፀባርቁ የከረሙት ተቃዋሚዎቻቸው እና ዴሞክራሲን የሚያቀነቅኑ አካላት ሙግት ለፕሬዚደንቱ ከቁብ የሚቆጠር አልሆነም፡፡

ይልቁኑ ሰውየው አሁንም በእድሜ እስካሉ በስልጣናቸው እንደሚቆዩ መግለፃቸው እየተደጋገመ መጥቷል፡፡

አሁን ግን በሃራሬ ከዚህ በተቃራኒው ተቃውሞው እያየለ የመጣ ይመስላል፡፡ ከወራት በፊት በተመረዘ ምግብ ሳቢያ የተጠረጠሩ የቤተመንግስቱ ሰዎች መመንጠራቸው እና ቀውሱም ለምክትሉ አለመታመን ምክንያት በመሆኑ ወዳጆቻቸው እየራቋቸው እንደሆነ ማሳያ ነው፡፡

የአገሪቱ ወታደራዊ ኃይል ከዚህ ቀደም አስፈላጊ ሆኖ ካገኘሁት ጣልቃ እገባለው ማለቱ የሚታወስ ሲሆን አሁን ግን እርምጃ መውሰድ መጀመሩ ነው እየተነገረ ያለው፡፡

የዚምባብዌ ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ዜድ ቢሲ  በወታደራዊ ኃይሉ በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡

የፕሬዚደንቱ መኖሪያ አካባቢም በወታደራዊ ኃይሉ ተከቧል፡፡ አንዳንድ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ያሉባቸው አካባቢዎች እና ዋና ዋና ጎዳናዎች በታጠቁ ወታደሮች ተሞልተዋል፡፡ በከተማውም አልፎ አልፎ የተኩስ ድምጽ ይሰማል፡፡

የሚሊታሪ ኃይሉ ዋና አዛዥ የሆኑት ጀነራል ኮንስታቲኒዮ ችዌንጋ እንዳሉት ፕሬዚደንቱ ደህንነታቸው እንደተጠበቀ ሲሆን ድርጊቱ መፈንቅለ መንግስት አይደለም ብለዋል፡፡

ድርጊቱ ወንጀለኞችን በቁጥጥር ስር ለማዋል የተካሄደ ነው ሲሉም ገልፀዋል፡፡ የመጀመሪያው የመንግስት የስራ ኃላፊው የፋይናንስ ሚኒስትሩን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ያነሳሉ፡፡

የብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያውም ህዝቡ እንዲረጋ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ የአሜሪካ ኤምባሲ ቢሮን ጨምሮ የውጭ አገራት ቢሮዎች እና አለማቀፍ ተቋማት ስራቸውን እንዳቋረጡእና በዝግ እየሰሩ ያሉም እንዳሉ ተገልጿል፡፡

የአሁኑ የዚምቧቡዌ ሁኔታ የመፈንቅለ መንግስት መልክ ቢኖረውም የወታደራዊ ኃይሉ ውድቅ ማድረጉን የመገናኛ ብዙሃኑ አጣጥለውታል፡፡

አንዳንድ ተንታኞችም ቢሆኑ የሙጋቤ የሥልጣን ዘመን ያበቃ ይመስላል ሲሉ ይተነትናሉ፡፡ ሙጋቤ 40 ዓመት በስልጣን ሰይቆዩ ሊነጠቁ ነው ብለው ሲሳለቁም ተደምጠዋል፡፡ (ምንጭ:  ከቢቢሲ፣ ሲ ኤን ኤን፣ አልጀዚራ እና ሮይተርስ)