የሚኒስትሮች ምክር ቤት የ14 ቢሊየን ብር ተጨማሪ በጀት አጽድቋል

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለተያዘው በጀት ዓመት የ14 ቢሊየን ብር ተጨማሪ በጀት አጽድቋል።

ምክር ቤቱ ትናንት ባካሄደው 9ኛ አስቸኳይ ስብሰባው በ2010 በጀት ዓመት የተጨማሪ በጀትና በሌሎች ሶስት ረቂቅ አዋጆች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል።

ምክር ቤቱ ባወጣው መግለጫ፥ ተጨማሪ በጀቱ በሀገሪቱ የሚደርስን የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ ለመከላከልና ለመቋቋም፣ የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ ቀሪ ክፍያን ለመሸፈን፣ የ11 አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎችን ቀጣይ የቅበላ አቅም ለማሳደግና የዲጂታል ቴሌቪዥን ሽግግርን ለማፈጠን የሚውል መሆኑን አስታውቋል።

የተጨማሪ በጀቱ በ2010 በጀት ዓመት የተቀመጡ የፕሮግራም በጀት ግቦችን ለማሳካት የበጀት እጥረት ያጋጠማቸውን አስፈጻሚ መስሪያ ቤቶችን ለመደጎም ይውላል ተብሏል።

በመሆኑም የሚኒስትሮች ምክር ቤት በቀረበው የተጨማሪ በጀት ረቂቅ አዋጅ ተወያይቶ በፌዴራል መንግስት ከሚገኘው ገቢ ላይ ለመደበኛ ወጪዎች 14 ቢሊየን ብር ወጪ ሆኖ ይፀድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል።

በሌላ በኩል ምክር ቤቱ ኢትዮጵያ ከዓለም ባንክ፣ ከፈረንሳይ የልማት ኤጄንሲ እና ከአፍሪካ ልማት ፈንድ ጋር ባደረገቻቸው ሶስት የብድር ስምምነት ረቂቅ አዋጆች ላይ ከተወያየ በኋላ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲፀድቅ መርቷል፡፡

ምንጭ- ኢቢሲ