በሰሜን ጎንደር ዞን ያለውን የኢንቨስትመንትና ቱሪዝም አማራጮችን መጠቀም እንዳልተቻለ ተገለጸ

በአማራ ብሔራዊ ክልል በሰሜን ጎንደር ዞን ያለውን ሰፊ የኢንቨስትመንትና ቱሪዝም አማራጮችን በአግባቡ መጠቀም እንዳልተቻለ  የዞኑ ተወላጅ ባለሃብቶች ገለጹ ።

በደባርቅ ከተማ  በተካሄደው የቱሪዝምና ኢንቨስትመንት ፎረም ላይ እንደተገለጸው  በሰሜን ጎንደር ዞን ሰፊ የሆነ  የቱሪዝምና ኢንቨስትመንት አማራጮች ቢኖሩም በአካባቢው በቂ የሆነ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ  ባለመከናወኑ ምክንያት ባለሃብቶቹ  በዘርፉ ገብተው ለመሥራት አልቻሉም ተብሏል ።

የሰሜን ጎንደር ዞን በዓለም አቀፍ ደረጃ የተመዘገቡ ባህላዊ ፣ታሪካዊ የቱሪስት መስህቦችና ቅርሶች ባለቤት መሆኑን የጠቆሙት የፎረሙ ተሳታፊዎች በዞኑ የሚገኘውን ሰፊ የኢንቨስትመንትና ቱሪዝም አማራጮች በአግባቡ መልማት ይገባዋል ብለዋል ።

በፎረሙ ላይ የሰሜን ጎንደር ዞን የቱሪዝምና ኢንቨስትመንት አመራጮችን በተመለከተ ሦስት  ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ወይይት ተደርጎባቸዋል ።

የሰሜን ጎንደር ዞን አካባቢ ተወላጅ ባለሃብቶች በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት በዞኑ በተለያዩ ዘርፎች የመሠማራት ፍላጎት ቢኖራቸውም በቂ የሆነ የመሠረተ ልማት አለመኖርና የሚሠጣቸው አገልግሎት አናሳ መሆኑን  አንስተዋል ።

በወይይቱ ወቅት  የተገኙት የኢፌዴሪ  የንግድ ሚንስትር  አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው በሠጡት ምላሽ እንደገለጹት በክልሉ በአጠቃላይ እንዲለሙ ከተመረጡት 280 የኢንቨስትመንት ዘርፍ አማራጮች ውስጥ 90 በመቶ የሚሆኑት  በዞኑ የሚገኙ መሆኑን አስረድተዋል ።

በሰሜን ጎንደር ዞን የሚታዩ የመሠረተ ልማት ችግሮችን ለመፍታትም  የጋራ የሆነ  የተቀናጀ አሠራርን  ለመከተል  መረባረብ እንደሚገባም  ተናግረዋል ።