የኢፌዲሪ ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የፌደራል ኦዲት መስሪያ ቤቶች ላይ የሚስተዋለውን የኦዲት ችግር ለመቅረፍ ከፌደራል መስሪያ ቤት ኦዲተሮች ጋር ውይይት አካሂደዋል፡፡
በውይይቱም የ2010 በጀት ዓመት የውስጥ ኦዲት አፈፃፀም የተገመገመ ሲሆን፤ በጠንካራና ደካማ ጎን የተስተዋሉ የኢዲቲንግ ስራዎች ተነስተዋል፡፡
የ2009 በጀት ዓመት የዋና ኦዲት መስሪያ ቤት የጥሬ ገንዘብ ጉድለት፣ ውዝፍ ሂሳብ፣ የተከፋይ ሂሳብ ለማን እንደሚከፈል አለመታወቅ የሚሉ እና ሌሎች ግኝቶች ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡
በዚሁም በ112 ተቋማት የ2009 በጀት ላይ በተደረገ ክትትል ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ የአላቂ እቃ ግዥ የተፈጸመና በ120 ተቋማት ደግሞ ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ በአላቂ ንብረቶች ፈሰስ እንዲካተት መደረጉን ነው የተብራራው።
በዚህም ተቋማቱ በጀት ከሚቃጠል በሚል በበጀት ዓመቱ መጨረሻ አካባቢ በርካታ ስልጠናዎችና ክፍያዎችን በመፈጸም ገንዘብ የሚያባክኑ መሆኑ ተገልጿል ።
አሁን ላይ በ2009 በጀት ዓመት የጎላ የኦዲት ግኝት ያለባቸው 61 ተቋማት ላይ ክትትሉ እየተደረገ መሆኑን ተጠቁሟል ፡፡
ከእነዚህም መካክል 38 ትምህርት ሚኒስቴርና እና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ 15 የኢኮኖሚ ልማት ዘርፎችና 13 የአስተዳደርና አገልግሎት ዘርፎች መሆናቸውም ታውቋል።
የ2011 የበጀት ዓመት የውስጥ ኦዲት እቅድ ላይ በጥናታዊ ፅሑፍ ተደግፈፎ ውይይት የተደረገ ሲሆን በባለፈው አመት የተስተዋለውን የኦዲት ችግር ለመቅረፍ አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ኦዲት መስሪያ ቤቶች ችግሮች እንዳለባቸው የተጠቆመ ሲሆን ክትትል እና ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ተሣታፊዎች አንስተዋል፡፡