በሶማሌ ክልል ቁፋሯቸው የተጠናቀቁ ሶስት የተፈጥሮ ጋዝ ማመንጫ ጉድጓዶች የሙከራ ምርት ጀመሩ

በቻይናው ፖሊ ጂሲኤል ፔትሮሊየም ሆልዲንግ የተባለው ኩባንያ በምስራቅ ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በቁፋሮ ላይ ካሉ የተፈጥሮ ጋዝ ማመንጫ ጉድጓዶች መካከል ሶስቱ ተጠናቆ ድፍድፍ ነዳጅ የሙከራ ምርት ትናንት ጀምሯል፡፡

የማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትር አቶ መለስ አለሙና የክልሉ ርስሰ መስተዳደር አቶ አብዲ መሐመድ የሙከራ ምርት የጀመሩትን ጉድጓዶቹን  መርቀዋል፡፡

የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ኢንጀነር እድሪስ ኢስማኤል  እንደገለጹት የሙከራ ነዳጅ ማውጣት ሥራቸውን የጀመሩት በጎዴ ዞን ኢላላ ወረዳና ቆራሃይ ዞን ሽላቦ ወረዳዎች ቁፋሯቸው የተጠናቀቁ ሶስት ጉድጓዶች ናቸው

ጉድጓዶቹ የሙከራ ምርት ስራቸውን በይፋ መጀመራቸው የክልሉ ህዝብ ለሰላም የከፈለው የመስዋእትነት ፍሬ ማሳያ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በምስራቅ ኢትዮጵያ ሲካሄድ የቆየው  የነዳጅ ፍለጋ ስኬታማ በመሆኑ ከዛሬ  ጀምሮ ኢትዮጵያ ድፍድፍ ነዳጅ የማምረት ሙከራ እንደምትጀምር   ከመጪው መስከረም አንስቶ በሁለት ዓመታት ውስጥ የሚጠናቀቅ  የነዳጅ ቱቦ ዝርጋታ ወደ ጂቡቲ እንደሚካሄድ  ከትናንት በስተያ  ይፋ ማድረጋቸውን በወቅቱ ተገልጿል።