”ኢትዮጵያዊያን እንደ እንቦጭ ሁሉን ለእኔ ብቻ ሳንል ለጋራ ጥቅም ልንሰራ ይገባል”–ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ

”ኢትዮጵያዊያን እንደ እንቦጭ ሁሉን ለእኔ ብቻ የምንል ሳይሆን ለጋራ ጥቅም ልንሰራ ይገባል” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን የርብ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክት የምርቃት ስነ-ስርዓት ላይ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጣና ሀይቅ የተንሰራፋው የእንቦጭ አረም እያደረሰ ያለውን ጉዳት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የክልል ፕሬዝዳንትና  ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ጎብኝተዋል።

“ኢትዮጵያ ለሁሉም የምትበቃ ለሌሎችም የምትተርፍ ስለሆነች በጋራ ኢጣልያንን እንዳሸነፍን፤ ዛሬም እንቦጭን በቴክኖሎጂ በመታገዝ ካለበት መሰብሰብ ያስፈልጋል” ብለዋል።

አሁንም ለኢትዮጵያዊያን የሚያዋጣው መደመር ብቻ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ”እንደ እንቦጭ ሁሉን ለእኔ ከሆነ ተያይዞ መጥፋት ብቻ ይሆናል” ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ለእርሻ ስራ ከቀደምቶቹ የምትመደብ ቢሆንም ግብርናን ከማዘመን ይልቅ የወረስነውን ይዘን ቆይተናል ከዘርፉም መጠቀም የሚገባንን ያህል አልተጠቀምንም ብለዋል።

የርብ መስኖ ፕሮጀክት ለአካባቢው አርሶ አደሮች መልካም አጋጣሚ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸው እንደ አገዳ፣ ጥራጥሬ፣ የቅባት እህል፣ ፍራፍሬ አትክልትና የአሳ ምርት በማምረት ለመመገብና ለመሸጥ ያስችላል ብለዋል።

ይህም ብቻ ሳይሆን የገጸ- ምድርና ከርሰ-ምድር ውሃችንን በተሰጠን ልክ ለመጠቀም የሚያስችል ፀጋ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የርብ ግድብ ፎገራ አካባቢ ለሚገኝ ሰፊ መሬት ማልሚያ ከመጥቀሙም ባለፈ በአካባቢው ያሉ አርሶ አደሮችንም ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል። (ኢዜአ)