ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከሳዑዲ የልማት ፈንድ ሊቀመንበር ጋር ተወያዩ

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከሳዑዲ የልማት ፈንድ ሊቀመንበር አሕመድ ቢን አቂል አል ካቲብ ጋር በሪያድ ተወያዩ።

በሳዑዲ የኢንቨስትመንት ፎረም ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ሪያድ የሚገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ  ከልማት ፈንዱ ሊቀመንበር ጋር ያደረጉት ውይይት በሁለቱ አገራት የምጣኔ ኃብት ትብብርና የወደፊት አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ ነው።

በውይይቱ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አክሊሉ ኃይለ-ሚካኤልና በሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደርና ልዩ መልዕክተኛ አብዱልአዚዝ አሕመድ ተገኝተዋል።

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ዘርፈ ብዙ ለውጥ እየተካሄደ መሆኑን  ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በውይይቱ ወቅት ገልጿል።

አገሪቱ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ቢኖርባትም ለውጡን ለማስቀጠል ከፍተኛ ጥረት እያደረገች መሆኑንም ጠቅሰዋል። እንዲሁም አገሪቱ ባለ ሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች መሆኗንም ገልፀዋል።

በተለይም የሥራ እድል ለመፍጠርና የአገሪቱን ልማትና ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማፋጠን መንግስት “ፈጠራ” ላይ ያተኮረ የልማት ፍኖት በመንደፍ ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን አቶ ደመቀ ጠቁመዋል።

ሊቀመንበር አሕመድ ቢን አቂል አል ካቲብ በበኩላቸው የሁለቱ አገራት ህዝቦች ወንድማማች መሆናቸውን ገልፀው፣ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ጠንካራ ሊባል የሚችል ግንኙነት እንዳላት ጠቁመዋል።

አገራቸው የኢትዮጵያን ብሔራዊ ልማት ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኗን ጠቁመው፣ የሳዑዲ አረቢያ መንግስት በውጭ ቀጥተኛ የኢንቨስትመንት ፍሰት ረገድ ከኢትዮጵያ ጋር ለመስራት ዝግጁ መሆኑንም አመላክተዋል።

ይህም የውጭ የኢንቨስትመንት ፍሰት ላይ አብሮ ለመስራት ፀጥታና ደህንነት ማስፈን እንዲሁም መረጋጋት መፍጠር እንደሚገባ ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያ በዚህ በኩል የተረጋጋች አገር በመሆኗ በመሰረተ-ልማት ዘርፎች ላይ አብሮ ለመስራት ፈቃደኝነታቸውን ገልፀዋል።

ከዚህ ቀደም የሳዑዲ ፈንድ ለተለያዩ የመሰረተ-ልማት አውታሮች ዝርጋታ፣ ግንባታና ማስፋፊያ ጉዳዮች ላይ ለኢትዮጵያ የፋይናንስ ድጋፍ እና እገዛ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰው፣ የሳዑዲ ፈንድ ተቋም ይህንን ተግባሩን በመቀጠል በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የልማት እንቅስቃሴዎችን እንደሚደግፍ ቃል ገብተዋል።

ሊቀመንበሩ በመቀጠል አንድ የመንገድ  የልማት ፕሮጀክት በኢትዮጵያ ወገን በኩል ለሳዑዲ ፈንድ ተቋም መቅረቡን ጠቅሰው፣ በቀጣይም የኢትዮጵያ መንግስት የፋይናስ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን የመሰረተ-ልማት ፕሮጀክቶችን ለሳዑዲ ፈንድ ተቋም በዝርዝር እንዲያቀርብ  ጠይቀዋል።

የሳዑዲ ፈንድ ተቋም በኢትዮጵያ ትምህርት ቤት ማስፋፋት፣ የሆስፒታልና የግድብ ግንባታ፣የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት፣ የፀሃይ ኃይልና ሌሎች የመሰረተ-ልማት ፕርጀክቶችን በፋይናንስ ለመደገፍ ሊቀመንበሩ ቃል የገቡ ሲሆን፣ የኢትዮጵያን የልማት ፕሮጀክቶች ከፋይናንስ ድጋፍ በተጨማሪ ብድር ለመስጠት ተቋሙ ዝግጁ መሆኑን ገልፀዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን ሳዑዲ አረቢያ በተለያዩ የጋራ ጉዳዮች ላይ እውነተኛና ቀዳሚ ወዳጅ አገር መሆኗን ገልፀው፣ በተለይም የኢትዮጵያን ልማት ለመደገፍ የምታደርገውን ጥረት እንደሚያደንቁ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በፀጥታው ዘርፍ በምታካሂደው መጠነ ሰፊና ጥልቅ የለውጥ እንቅስቃሴ እንዲሁም የዶክተር አብይ አሕመድ የመደመር ንፅረተ-ዓለም ትልም ዳር መድረስ የሳዑዲ አረቢያ እገዛ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ የጀመረችውን ሁሉን አቃፊና አካታች ለውጥ ለማስቀጠል በምታደርገው ጥረትና በአፍሪካ ቀንድ የምታደርገውን አዎንታዊ ሚና እንደሚያግዝም ገልፀዋል።

የኢትዮ-ኤርትራ እርቅ በቀጠናው አዲስ እድል ይዞ የመጣ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰው፣ የሳዑዲ አረቢያ መንግስት የሁለቱ አገራት መሪዎች ለሰላምና ወዳጅነት ላሳዩት ዲፕሎማሲያዊ ብልሃትና ጥበብ እውቅናና ምስጋና መስጠቱ በጎ የዲፕሎማሲ ምግባር ሊባል የሚችልና ወዳጅነትን የሚያጠናክር ተግባር መሆኑን ጠቁመዋል።(ኢዜአ)