ሚኒስቴሩ በአንደኛው ሩብ አመት 124 ህገወጥ ድርጅቶች በንግድ ሥርዓት ውስጥ ሲንቀሳቀሱ ማግኘቱን አስታወቀ

የገቢዎች ሚኒስቴር በ2011 ዓ.ም አንደኛ ሩብ አመት 1 መቶ 24 ህገ-ወጥ ድርጅቶች በንግድ ሰርዓት ውስጥ ሲንቀሳቀሱ መገኘታቸውን አስታውቋል፡፡

ድርጅቶቹ የነፃ ንግድ ውድድር ሥርዓቱን በመጣስ ከአራት ቢልዮን ብር በላይ ግብይት መፈፀማቸውን በገቢዎች ሚኒስቴር የህግ ማስከበር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዘመዴ ተፈራ ተናግረዋል፡፡

በተያያዘም ከሀገር ውስጥ በግብር መልክ መሰብሰብ ከነበረበት 3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ በሩብ ዓመቱ ሳይሰበሰብ መቅረቱ ተገልጿል፡፡

እስከ ጥቅምት 30፤ 2011 ዓ.ም ባለው ጊዜ 67 በመቶ የሚሆኑ የንግድ ድርጅቶች በኪሳራ፣ ፍቃድ ተመላሽ በማድረግ እና ቀጥታ ወደ ስራ ባለመግባት በንግድ ሥርአት ውስጥ ተሳትፎ አለማድረጋቸውን ተቋሙ ባደረገው ጥናት ማረጋገጡን ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል፡፡

በሓሰተኛ ማንነት በድርጅት ስም ሲንቀሳቀሱ የተደረሰባቸው 124 ድርጅቶች  ስም ዝርዝራቸውን በቀጣይ ህዝቡ እንዲያውቃቸው  ይፋ የሚደረግም መሆኑ ተገልጿል ፡፡

ወጪን በመቀነስና ገቢን በማሳነስ ያለአገልግሎት ግብይት የተፈፀመ በማስመሰል ሀሰተኛ ሰነድ የሚያቀርቡ ህግ ወጥ ድርጅቶች ላይ በቀጣይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስታውቋል፡፡