ምክር ቤቱ የቋሚ ኮሚቴ አመራርና አባላት ምደባን በተመለከተ የቀረበውን የውሣኔ ሃሣብ ዳግም በመመርመር አፀደቀ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው ልዩ ስብሰባ የቋሚ ኮሚቴ አመራርና አባላት ምደባን በተመለከተ የቀረበውን የውሣኔ ሃሣብ ዳግም በመመርመር አጽድቋል ።

ምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎቹን በሰብሳቢነት እንዲመሩ የተመደቡ አመራሮች ላይ በተናጠል ድምጽ በመስጠት ነው  የውሳኔ ሃሳቡን ያፀደቀው፡፡

የስምንቱ እጩ የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች ምደባ በአብላጫ ድምፅ ሲጸድቅ የሁለቱ ግን ውድቅ መሆኑ ተገልጿል፡፡ በዚህም መሠረት ፡-

1.ወይዘሮ አበባ ዮሴፍ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ- ሰብሳቢ

2.ወይዘሮ ፎዚያ አሚን ህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ-ሰብሳቢ

3.አቶ መሐመድ የሱፍ የመንግስት ወጪ አስተዳደርርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ-ሰብሳቢ

4.ወይዘሮ እምዬ ቢተው የሠው ሀብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ- ሰብሳቢ

5.አቶ ጌታቸው መለስ ንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ-ሰብሳቢ

6.ወይዘሮ አልማዝ መሰለ የግብርናና አርብቶ አደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ-ሰብሳቢ

7.ወይዘሮ ፈቲያ የሱፍ የተፈጥሮ ሀብት መስኖና ኢነርጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ-ሰብሳቢ

8.አቶ አሸናፊ ጋዕሚ የኮንስትራክሽን እና ትራንስፖርት ጉዳች ቋሚ ኮሚቴ-ሰብሳቢ በመሆን በምክር ቤቱ አባላት ተመርጠዋል፡፡

ሆኖም የውጭ ግንኙነትና የሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሰብሳቢነት እንዲመሩ በእጩነት ቀርበው የነበሩት አቶ ሞቱማ መቃሳ በ109 ድጋፍ፣ በ152 ተቃውሞ እና በ33 ድምፀ ተዓቅቦ  ሳይፀድቅ ቀርቷል፡፡

እንዲሁም ለገቢዎችና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሰብሳቢነት እንዲመሩ በእጩነት ቀርበው የነበሩት አቶ አፅብሃ አረጋዊ በ102 ድጋፍ በ157 ተቀውሞ በ25 ተዓቅቦ በተመሳሳይ እንዳልተመረጡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታውቋል፡፡

ምክር ቤቱ ባለፈው ጥቅምት 27 ቀን 2011 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የቀረበለትን የቋሚ ኮሚቴ አመራርና አባላት ምደባን የውሳኔ ሓሳብ ሳያጸድቅ መቅረቱ የሚታወስ ነው።

በተያያዘ ዜና የፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ “የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ አቶ አየለ ዲቦ ከባድ የዲሲፕሊን ጥሰት ፈጽመው አግኝቻቸዋለሁ” ሲል በዳኛው ላይ  የስራ ስንብት ውሳኔ እንዲተለፍለት ለምክር ቤቱ  አቅርቧል።

ስልጣንና ክብርን በመጠቀም ፍትህን ማዛባት ደግሞ ጉባኤው በዳኛው ላይ ያቀረበው ዋነኛ የዲሲፕሊን ግድፈት ነው።

ምክር ቤቱም  የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ ለህግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።