በአገራችን 52 በመቶ የሚከሰተው ሞት ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች መሆኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስተወቀ

የኢፌዴሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ በአገራችን ከሚከሰተው ሞት 52 በመቶ የሚሆኑት መንስኤያቸው ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መሆናቸው አስታውቋል፡፡

ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በተለይም ከልብና ደም ስር ጋር የተያያዙ ህመሞች፣ ካንሰር፣ የስኳር በሽታ እና ከመተንፈሻ አካላት ጋር የተያያዙ ህመሞች በከፍተኛ ደረጃ እየጨመሩና በአለማችን የህመም፣ የሞትና የአካል ጉዳት መንስኤ እየሆኑ መምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡

ለሽታዎቹ መባባስ ድህነት፣ የከተሞች መስፋፋት እንዲሁም የሰዎች አመጋገብና አኗኗር ዘይቤ ለውጥ እንደመንስኤ ተጠቅሷል፡፡

በዚሁም ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ፣ በቂ ያልሆነ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፣ አልኮል አብዝቶ መጠቀም፣ ትምባሆ ማጨስ፣ ጫት መቃም እና ሌሎች እጾችን መጠቀም በጤና ላይ ጉዳት እንደሚያደርስም ተጠቁሟል።

ሚኒስቴሩ የችግሩን ግዝፈት በመገንዘብ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችንና አጋላጭ መንስኤዎቻቸውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ርብርብ እያደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡

ለተግባራዊነቱ እንዲያመች የከተማ መንገዶችን በተወሰነ መጠን ከተሽከርካሪ ፍሰት ነፃ በማድረግ የሚከናወን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችንና አጋላጭ መንስኤዎቻቸውን የመከላከልና መቆጣጠር መርሃ ግብር ማዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡

ከተሽከርካሪ ነፃ በሚሆኑ የተመረጡ መንገዶች ላይ የአካል እንቅስቃሴዎች፣ ተላለፊ ላልሆኑ በሽታዎች ነፃ ምርመራዎች እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች “ጤናማ የአኗኗር ዜይቤ ለጤናማ ሕይወት” በሚል መሪ ቃል እንደሚከናወን ተገልጸዋል፡፡

ይህ ፕሮግራም ለጊዜው በአዲስ አበባ ከተማ ተግባራዊ የሚሆን ሲሆን በሂደት ወደ ሌሎች የአገሪቱ ትላልቅ ከተሞች እንዲሰፋ የሚደረግ ነውም ተብለዋል፡፡ (ምንጭ፡-የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር)