በቤኒሻንጉል ጉምዝና በኦሮሚያ ክልሎች አጎራባች አካባቢዎች የፀጥታ ችግር የሚፈታ ኮማንድ ፖስት ተቋቋመ

በቤንሻንጉል ጉሙዝና በኦሮሚያ ክልሎች አጎራባች አካባቢዎችን የጸጥታ ችግር የሚፈታ ኮማንድ ፖስት ተቋቋመ፡፡

የኮማንድ ፖስቱ አባል አቶ ሰይፈዲን ሐሩን ለኢዜአ እንዳስታወቁት ኮማንድ ፖስቱ የፌደራልና የሁለቱ ክልሎች መንግሥታት፣ የአገር መከላከያ ሠራዊትና ፌዴራል ፖሊስን ያቀፈ ነው፡፡

ኮማንድ ፖስቱ የተቋቋመው በክልሎቹ አጎራባች አካባቢዎች የመሸገውን የታጠቀ ኃይል በመቆጣጠር የኅብረተሰቡን ደህንነት ለማስጠበቅ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡  

መቀመጫውን በአሶሳ ከተማ  የሚያደርገው ኮማንድ ፖስቱ፣ ከሱዳን የጸጥታ ኃይሎች ጋር ተባብሮ እንደሚሰራ አቶ ሰይፈዲን ገልጸዋል፡፡                              

በቤኒሻንጉልና በኦሮሚያ ክልሎች አጎራባች አካባቢዎች ባለፉት ሦስት ወራት በተከሰተ የጸጥታ ችግር ከ100 በላይ ሰዎች ሲሞቱ፣ በ10 ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች መፈናቀላቸው ይታወሳል፡፡(ኢዜአ)